በዞኑ በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለውጭ ምንዛሬ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚውሉ ሰብሎች ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለውጭ ምንዛሬ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚውሉ ሰብሎች ትኩረት ተሰጥቷል
ገንዳ ውሃ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለውጭ ምንዛሬ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለሚውሉ ሰብሎች ይበልጥ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የ2018/19 ዓ.ም የመኸር እርሻ የሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሄዷል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በመጪው ክረምት በሚካሄደው የሰብል ልማት ሥራ ምርታማነትን ለማሳደግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
በዞኑ በምርት ዘመኑ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 530 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ውስጥ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ለውጭ ምንዛሬና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውሉ ሰብሎች እንደሚለማም ተናግረዋል።
እንደ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ጥጥ እና ሱፍ ያሉ ሰብሎችን በሜካናይዝድ እርሻ በማልማት በአጠቃላይ ከ12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት 219 አዳዲስ ትራክተሮች ወደ ዞኑ እንደገቡ የገለጹት አቶ አንዳርጌ፣ በዚህም የሜካናይዝድ እርሻን በማስፋፋት የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት በትጋት ይሰራል ብለዋል።
በየደረጃው ያለው የግብርና ባለሙያና አመራሩ ለአርሶ አደሩና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሰራም አሳስበዋል።
የቋራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አስማረ አንዳርጋቸው ፤ በ2018/19 የመኸር እርሻ 154 ሺህ 817 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የማሳ ዝግጅትና የጽዳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በአይነት፣ በብዛትና በጥራት ለማምረት ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።
የመተማ ወረዳ ዋና አስተሳዳዳሪ አቶ ግዛት ሰረፀ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በወረዳው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አስፈላጊ ግብአቶች እንዲሟላ እየተደረገ ነው።
በዞኑ ለግብርና ልማት የተሰጠው ትኩረት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ልማት መፋጠንና ለውጭ ገበያ የምረት አቅርቦት ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።