ቀጥታ፡

ታሪካችንን በራሳችን አንደበት የምንነግርበት ጊዜ አሁን ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ ታሪካችንን በራሳችን አንደበት የምንነግርበት እና የምንሰንድበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን በባለቤትነት ለመምራት ያለመው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል።

ጉባኤው  አፍሪካውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በአንድ መድረክ በማገናኘት በአህጉራቸው የጋራ ትልሞች ላይ እንዲመክሩ የሚያስችል መድረክ ነው፡፡

የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ከአራቱም የአህጉሪቷ ማዕዘናት በመምጣት በውቧ አዲስ አበባ ከትመው የተለየዩ የልማት ሥራዎችን መጎብኘት ጀምረዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን የመጣችው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ አዲት ሱዛን ሰዎች ብዙ ጊዜ የአፍሪካን መጥፎ ገፅታ እንጂ ያላትን አቅም፣ ጸጋና በረከት አይናገሩም ብላለች፡፡

አፍሪካ ከዓለም ማዕዘናት ሁሉም ሊጎበኟት የሚገባ ውብ አህጉር መሆኗን በመጥቀስ፤ ጉባኤው የአህጉሪቱ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ወደ አንድ ማምጣቱ ያጋራ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጻለች፡፡

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ጉባዔ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን አንድ ማድረግ ያስችላል ብላለች፡፡

ማላዊያዊው ኬቨን ጉምቢ (KBG)፤ አፍሪካ ሁሉም ሀብቶች፣ የሚያምሩ ታሪኮች እና የውብ ጥበቦች አድባር የሆነች አህጉር መሆኗን ገልጿል፡፡

ብዙውን ታሪካችንን ሌሎች ሲነግሩን ቆይተዋል ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪው፤ ታሪካችንን በራሳችን አንደበት የምንነግርበትና የምንሰንድበት ጊዜ አሁን ነው ብሏል፡፡

የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ይዞት የመጣው ሀሳብ ግሩም መሆኑን የገለጸው ደግሞ ከዩጋንዳ የመጣው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ሞሰስ ኬዩኔ ነው።

አፍሪካውያን በዚህ መንገድ መገናኘታቸው እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ባህላቸውን እንዲጋሩ እና እንዲያሳድጉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጿል።

የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ እርስ በእርስ ለመማማር እና ልምድ ለመለዋወጥ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም