ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ ነው

ወልቂጤ፣ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡

ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ ምሁራን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የነበራትን የባህር በር መልሶ ለማግኘት በሚደረገው ጥረት የመንግስትን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በጥናትና በምርምር ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተውታል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ያለ ህዝብ ይሁንታ ለዘመናት ትጠቀምበትና ትታወቅበት የነበረውን የባሕር በር በሴራ ማጣቷን ነው የሚገልጹት፡፡

በመሆኑም የባሕር በር ጥያቄ ተገቢና ፍትሃዊ በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኝ መንግስት የጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ምሁራን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ስራችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ልማት መምህርና ተመራማሪ ኢንጂነር ቀነኒ ኤልያስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የትውልድ ቁጭት መሆኑን ጠቅሰው ህጋዊና ታሪካዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባህር በር አልባ መሆን ኢኮኖሚያዊና የደህንነት ህልውናን የሚፈትን በመሆኑ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ለጀመረው ጥረት የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡ 

የኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ የሆነው የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሁሉንም የጋራ ጥረት ይጠይቃል ያሉት ደግሞ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ መምህርና ተመራማሪ ስለሺ ታመነ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የባህር በር ጥያቄው ምላሽ ማግኘት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መገንባት እንድትችልና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስናና አገልግሎት መምህርና ተመራማሪ እድሜዓለም ተመስገን፤ ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ጭምር ነው ብለዋል።

የባህር በር ጉዳይ ከኢኮኖሚና ማህበራዊ ጠቀሜታውም ባሻገር የደህንነትና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጥያቄው ለውጤት እንዲበቃ አንድነትን በማጠናከር መንቀሳቀስ እንደሚገባ አመልክተው ምሁራንም በጥናትና ምርምር የተደገፈ አበርክቷችንን ማጎልበት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም