ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፍ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ግንባር ቀደም ሚና እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፍ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ግንባር ቀደም ሚና እየተወጣ መሆኑን የኤርባስ የአፍሪካ አየር መንገድ ኃላፊ ገለጹ።

ምርትና አገልግሎትን ለዓለም ገበያ በማድረስም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንግድና ኢንቨስትመንትን እያፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ከሊፋ ሁሴን ተናግረዋል።

የኤርባስ የአፍሪካ አየር መንገድ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ዩፕ ኢለርስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአቬሽን ኢንዱስትሪ የአህጉራትን ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በማሳለጥ ወሳኝ ሚና የሚወጣ ዘርፍ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ባለፉት 80 ዓመታት የበረራ አገልግሎት አፍሪካን ከቀሪው ዓለም እያስተሳሰረ የሚገኝ አንጋፋ አህጉራዊ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የአፍሪካን ምርትና አገልግሎቶች በዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ንግድና ኢንቨስትመንትን እያበረታታ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የበረራ አድማሱን እያሰፋ መምጣቱም የአፍሪካን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በማሳለጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጠው የእንግዳ ተቀባይነት መስተንግዶም የሚደነቅ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከበረራ አገልግሎት ባሻገርም በአውሮፕላን ጥገና፣በትምህርትና ስልጠና የአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ዕድገት መገለጫነቱን የሚያሳልጥ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ኤርባስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር በአቪዬሽን ስልጠና በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ከሊፋ ሁሴን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ምልክት ነው ብለዋል።

የአየር መንገዱ የበረራ አድማስ እየሰፋ መምጣትም ምርትና አገልግሎትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም