በምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ የለማ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያን ለማረጋጋት አግዟል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ የለማ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያን ለማረጋጋት አግዟል
አዳማ ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ የለማ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ገበያን ለማረጋጋት ማገዙን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወቅት ባህላዊና ዘመናዊ መስኖን በመጠቀም ከ63 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ለምቷል።
የአዋሽ ወንዝን በመጥለፍና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም በስፋት ከለሙት አትክልቶች መካከል ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ድንችና ሌሎችም የስራስር ምርቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ከፍራፍሬ ምርቶች መካከልም ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ እና ሀብሀብ ዋንኞቹ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዚህም በመጀመሪያ ዙር ከለማው አትክልትና ፍራፍሬ ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ምርት ገበያን በማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው ለአርሶ አደሩም የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ስርአተ ምግብን ለማሻሻል ማገዙን ገልጸዋል። እንዲሁም ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራ አይነተኛ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
በበጋ መስኖ ልማቱ ከ35 ሺህ በላይ ወጣቶችና አርሶ አደሮች መሳተፋቸውንም አስታውቀዋል።
በዞኑ የገፀና ከርሰ ምድር የውኃ ሀብትን በመጠቀም 2ኛው ዙር የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ልማት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል ።