ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ጉዞ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ጉዞ አጠናክሮ ይቀጥላል
ቀብሪ ደሃር፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ በሶማሌ ክልል ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ጉዞ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱራህማን አህመድ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ በሶማሌ ክልል ቆረሃይ ዞን ቀብሪ ደሃር ከተማ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያደርገውን የምርጫ ቅስቀሳ እና የማኒፌስቶ ማስተዋወቅ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት አካሄደ።
በዝግጅቱ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና የከተማዋ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ ፓርቲው በቀጣይ ዓመታት ይዞአቸው የተነሳቸውን የልማትና የፖለቲካ ግቦች ይፋ አድርጓል።
በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱራህማን አህመድ ፤ በክልሉ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የልማት ዕቅዶች በዋናነት ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፓርቲው በሀገሪቱ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ይበልጥ በማዘመንና የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማስቀጠል፣ ብልጽግናን በተጨባጭ እውን የሚያደርጉ ስልታዊ ዕቅዶችን ቀርጾ ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
የቆረሃይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻፊ ሙሁመድ በበኩላቸው፤ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በተከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ጥራት ጠብቀው በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በፍጥነት እየተገነቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በከተማው በተካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃግብር ላይ የፓርቲው ደጋፊዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።