በአማራ ክልል የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባህር ዳር ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ ከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር በተለያዩ አማራጮች የመፍታት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በዚህም በማህበራት እና በጋራ የቤት ልማት የተደራጁትን ጨምሮ ሪል ስቴት ቤት ለመገንባት ለፈለጉ ዜጎች እንደየ ሁኔታው ታይቶ የግንባታ ቦታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ140 ሺህ ለሚልቁ ግለሰቦችና ማህበራት ቤት መስርያ ቦታ በመስጠት ወደ ቤት ልማት ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 51 ሺህ 460 የመኖሪያ ቤቶች በግል አልሚዎች፣ በማህበራት፣ በሪልስቴት እና በመንግስት መገንባታቸውን ነው የገለጹት።
በዚህ በጀት ዓመትም ከ288 ሺህ በላይ ዜጎች በማህበር በመደራጀት ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል ቦታ መውሰድ እንዲችሉ ቅድመ ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ገልፀዋል።
አባላቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ የቻሉ ሲሆን ከ5 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት እየተዘጋጀ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅትም ለአንድ ሺህ 12 ማህበራት የግንባታ ቦታ ማስረከብ የተቻለ መሆኑን ጠቁመው ቀሪ ማህበራትን ተጠቃሚ ለማድረግም የመረጃ ማጥራትን ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ማህበራቱ በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ትኩረት እንዲያደርጉ እየተደረገ ሲሆን ይህም መሰረተ ልማት ለማሟላትም ሆነ የግንባታ ቁሳቁሶችን በቡድን ለመጠቀም ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
በተለይም አዳዲስ በሚለሙ መንደሮች የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት እና መሰል መሰረተ ልማት ፈጥነው እንዲሟሉም ትኩረት መደረጉን አብራርተዋል።
የቤት ግንባታዎች የከተሞችን ዘላቂ እድገት መሰረት ባደረገ የግንባታ ፕላን መሰረት እንዲከናወኑም አስፈላጊ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።