በምርጫው ሂደት ለዜጎች ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻችንን እየተወጣን ነው-የሴቶች ፌዴሬሽን እና ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ሂደት ለዜጎች ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻችንን እየተወጣን ነው-የሴቶች ፌዴሬሽን እና ማህበራት
አምቦ ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በምርጫው ሂደት ዜጎች በቂ ግንዛቤ ይዘው ድምፃቸውን ለመስጠት የሚያስችል ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የአምቦ ከተማ የሴቶች ፌዴሬሽን እና የሴቶች ማህበር ገለጹ።
የ7ኛው ጠቅላላ የምርጫ ሂደት ቀጥሎ ፓርቲዎች ራሳቸውን እያስተዋወቁና የምረጡኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ ይገኛሉ።
መራጮችም ከፓርቲዎቹ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመነሳት ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል የሚሉትን ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ናቸው።
በመሆኑም ዜጎች የተሻለ ግንዛቤ አግኝተው በምርጫው በመሳተፍ መብታቸውን እንዲጠቀሙ በማስገንዘብ ረገድ የሲቪል ማህበራት ሚና የማይተካ ነው።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሠማሩ 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መስጠቱ ይታወቃል።
በአምቦ ከተማ በዚሁ ተግባር ላይ ከተሰማሩት ድርጅቶች መካከል የኢዜአ ሪፖርተር የሴቶች ፌዴሬሽን እና የሴቶች ማህበርን አነጋግሯል።
የሲቪል ማህበራቱ ሃላፊዎችም በምርጫው ሂደት ዜጎች በቂ ግንዛቤ ይዘው ድምፃቸውን ለመስጠት የሚያስችል ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
የአምቦ ከተማ የሴቶች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ወይዘሮ ድንበሬ ጥበቡ፤ የፌዴሬሽኑ አባላት ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ባለመወገን በገለልተኝነት ለማገልገል ቃል ገብተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫ ሥነ-ምግባር ህጎች ዙሪያ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ለአባላቱ የተሟላ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ ስለመሆናቸውም አረጋግጠዋል።
የአምቦ ከተማ የሴቶች ማሕበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ሶስና ዲበኩሉ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ሴቶች በመምረጥ፣ በመመረጥና በምርጫ ታዛቢነት ሂደት በመሳተፍ ሚናቸውን እንዲወጡ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት ማህበሩ ከሌሎች የሲቪክ ማህበራት ጋር በመቀናጀት እንዲሁም ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ሀገራዊ አደራውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ በመርሃ ግብር መያዙ ይታወቃል።