በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ68 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ68 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል
ቦንጋ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ68 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን ታቅዶ የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሀገሪቱ ከፍተኛ የደን ሽፋንና የተፈጥሮ ሀብት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።
ክልሉ በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚያከናውናቸው የችግኝ ተከላ ስራዎች፣ ነባር ደኖችን ከመጠበቅ ባለፈ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማትና የብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የ68 ሺህ ሄክታር መሬት ሽፋን ዕቅድም ይህንን ክልላዊና ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም ስትራቴጂ አካል ያደረገ ነው።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደገለጹት፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
ለዚህም ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች የማዘጋጀትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የተከላ ቦታ ልየታና መረጃ የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ68 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደንና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች ለመሸፈን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ምክትል ሀላፊና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታሪኩ ወልደ ሚካኤል በበኩላቸው፣ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ዝግጅት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በዞኑ የፍራፍሬ፣ የሻይ፣ የቡናና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም በ539 የችግኝ ጣቢያዎች ዘር የማፍሰስና የችግኝ እንክብካቤ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተዘጋጁ ችግኞችም በ36 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚተከሉ ሲሆን ቦታ የመለየት እና መረጃ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
አርሶ አደሮችም፣ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ገልፀው፣ የመርሃግብሩ መጀመር ደንን በአግባቡ ለመጠበቅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ተከላ መርሃግብር የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
የሚተከሉ ችግኞች ፀድቀው አገልግሎት እንዲሰጡ መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት አርሶአደሮቹ ፣ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ጥቅም እያገኙ እንደሆነም ገልፀዋል።