በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው
ደሴ ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ የተመለከቷቸው የልማት ስራዎች ለህዝብ ጥያቄ ምላሽን ከመስጠት ባሻገር ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ።
የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮቹ እንደገለፁት፤ በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
"የሰላም ለኢትየጵያ ጥምር ፓርቲ" የምርጫና ፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊና የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዚዳንት አቶ አላምረው ይርዳው፤ የኢትየጵያ ህዝብ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት የሚረጋገጠው በሚገነቡ የልማት ስራዎች ትስስር ነው ብለዋል።
በደሴ ከተማ የተመለከትነው የልማት ስራ ህብረተሰቡን በተግባር ተጠቃሚ ያደረገ፣ ለዘመናት የልማት ጥያቄ መልስ የሰጠና የቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የኮሪደር ልማት፣ ስማርት ሲቲ፣ የአስፋልት መንገድና ሌሎች የልማት ስራዎች ልምድና ተሞክሮ ሊወሰድባቸው የሚገባ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የእኛ ህልም፣ ራዕይና ሀሳብ ህብረተሰቡ በልማትና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ሲሆን ማየት ነው ያሉት ደግሞ የወሎ ህዝቦች ዲሞክራሲ ፓርቲ የምርጫና ዴሞክራሲ ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ የሺበር ጌጡ ናቸው።
በደሴ ከተማ የተመለከትነው የልማት ስራም አስደናቂና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ በመሆኑ ተደስተናል፣ በሌሎች አካባቢዎችም እንዲደገም እንፈልጋለን ብለዋል።
የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቦርድ አባል አቶ ዮሴፍ አሻግሬ በበኩላቸው፤ በደሴ ከተማ በተመለከትነው የልማት ስራ የአመራሩ፣ የባለሙያውና የህብረተሰቡ ቅንጅት ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህም የዘመናት የልማት ጥያቄን ለመመለስ ውጤታማ የልማት ስራዎችን በማከናወን ከተማዋን ለቱሪዝም፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ የከተማውን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ህብረተሰቡን በማስተባበር ሰፋፊ የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ቀርፏል ያሉት አቶ ሳሙኤል በኮሪደር ልማት፣ በአስፋልት መንገድና በስራ እድል ፈጠራ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በከተማው የተሰሩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸው እየመጣ ያለውን ቀጣይነት ያለው ለውጥ ተገንዝበው ለልማት ያላቸውን ትብብር እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የደሴ ከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።