ዲጂታል አገልግሎት የአሰራር ዘመናዊነትን እና የምርታማነት እድገትን በተጨባጭ እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል አገልግሎት የአሰራር ዘመናዊነትን እና የምርታማነት እድገትን በተጨባጭ እያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የዲጂታል አገልግሎት አሰራርን በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርን በመከላከልና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብሯ አማካኝነት ቴክኖሎጂን ለዘላቂ እድገት እንደ ዋና መነሻ በመጠቀም ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በዚህም ኢኮኖሚውን የሚያሳልጡ የዲጂታል ዘርፍ ስራዎች በስኬት እየተከናወኑ ነው።
በተለይም እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ፋይዳ መታወቂያ እና ኢትዮ-ኮደርስ ያሉ መድረኮች መዘርጋታቸው እንዲሁም የኢንተርኔት ተደራሽነት መጨመሩ ለሀገራዊ ለውጡ ትልቅ ፋይዳ አለው።
እነዚህ የቴክኖሎጂ ስኬቶች የሞባይል ክፍያና የኢ-ኮሜርስ ስርዓትን በማቀላጠፍ፣ የተገልጋዮችን ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ ተብራርቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂ አሰራርን በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርን በመከላከልና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና አለው፡፡
አዲስ አበባን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በተነደፈው የስምንት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አማካኝነት በኮሪደር ልማትና በመዝናኛ ስፍራዎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
የስማርት ሲቲ ግንባታ ዋና ዓላማ ከተማዋን ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ምቹና ሳቢ ማድረግ ሲሆን፣ ይህም የሚረጋገጠው አገልግሎቶችና መሰረተ ልማቶች በቴክኖሎጂ ሲደገፉ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም በከተማዋ የተከናወኑ ስኬታማ የቴክኖሎጂ ስራዎች ከንቲባ አዳነች አቤቤ እ.ኤ.አ በ2024 በደቡብ ኮሪያ ሴዑል በተካሄደው የዓለም አቀፍ ስማርት ሲቲ አመራር ውድድር አሸናፊ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ተግባራት መዲናዋ በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ስማርት ሲቲ ፎረም ላይ ተገቢውን እውቅና እንድታገኝ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ነው ያሉት።
የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት አገልግሎታቸውን በዲጂታል መንገድ እንዲያቀርቡ ለማስቻል፣ ቢሮው የቴክኖሎጂ ስርዓቶችን የማበልጸግ፣ የማቀናጀትና ደህንነታችውን የማስጠበቅ ስራዎችን ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የወረዳ ኔት መሠረተ ልማትን ወደ ሲቲ ኔት በማሳደግ በከተማዋ የሚገኙ ወረዳዎችንና ክፍለ ከተሞችን በቴክኖሎጂ ማስተሳሰር ተችሏል ብለዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን፣ ተአማኒ፣ ፍትሐዊና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ የተገልጋዮችን እንግልት በመቀነስና ግልጽነትን በመፍጠር፣ ህብረተሰቡ በዲጂታል አማራጮችን የመጠቀም ልምዱ እንዲዳብር ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም ወደ ዲጂታል ሥርዓት ያልገቡ አገልግሎቶችን የማዘመንና ወደ "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማስገባት ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታውቀዋል።