ቀጥታ፡

አገልግሎቱ ለአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አዳዲስ የዲስትሪቢዩሽን መስመሮች ማስፋፊያ አከናወነ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት ዘጠኝ ወራት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ባከናወነው ሥራ 9 ሺህ 588 ኪሎ ሜትር አዳዲስ የዲስትሪቢዩሽን መስመሮች ማስፋፊያ (ዝርጋታ) አከናወነ፡፡

በዚህም መሠረት 3 ሺህ 518 ኪሎ ሜትሩ የመካከለኛ መስመር ቀሪው ደግሞ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ የተከናወነበት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኃይል አቅርቦቱን የሚያሳድጉ 3 ሺህ 683 የተለያየ ዐቅም ያላቸው አዲስ የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ተከላ መከናወኑን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።

ነባሩን የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ዐቅም ከማሻሻልና የኃይል መቆራረጥን ከመቀነስ አኳያም፤ 62 ሺህ 274 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመካከለኛ መስመር እንዲሁም በ67 ሺህ 131 ትራንስፎርመሮች ላይ የቅድመ መከላከል ምርመራ ተካሂዷል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 99 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ መስመር መልሶ ግንባታ መከናወኑን ጠቁመው፤ በ1 ሺህ 579 ነባር የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ላይ የዐቅም ማሻሻያ መሠራቱን አስታውቀዋል።

ለኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መንስዔ የሆኑ ምክንያቶችን በጥናት ከመለየትና እርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ፤ያረጁ መስመሮችን መልሶ የመገንባት፣ዐቅም የማሳደግና የማሻሻል እንዲሁም በዋናው ግሪድና በፀሐይ ኃይል አማራጭ አዳዲስ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማትን በከፍተኛ ወጪ እየተገነባ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም