ቀጥታ፡

በከተማዋ ለባለይዞታዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጂታል ካርታ እየተዘጋጀ ነው

ጎንደር ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ ከ45 ሺህ በላይ የቤትና የቦታ ባለይዞታዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጂታል ካርታ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን የከተማዋ መሬት መምሪያ አስታወቀ።

የዲጂታል ካርታው አሰራር በመሬት አስተዳደር ዙሪያ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታትና ዘመናዊ አሰራርን ለማስፈን ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

የከተማው መሬት መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አዛናው መልካሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዲጂታል ካርታው በዘርፉ የሚስተዋለውን የነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ከመሠረቱ በሚፈታ መልኩ እየተከናወነ ነው።                                                  

በስድስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የቤትና የቦታ ይዞታዎችን ወደ ዲጂታል የካርታ አሰራር ስርአት ለመቀየር መረጃን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በማጣራት ወደ መረጃ ቋት የማስገባት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከአራት ሺህ በላይ የከተማ ቦታና ቤት ባለይዞታዎችን በመመዝገብ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ባለይዞታዎች ዲጂታል ካርታ ማስረከብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል ካርታው ህጋዊነቱ የተረጋገጠ ይዞታ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ ቀደም ሲል ይፈጸሙ የነበሩ በካርታ ላይ ካርታ የመስጠት፣ መረጃ የማጥፋትና የስርቆት ድርጊቶችን ለማስቀረት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከልና ውድ ሃብት የሆነውን መሬት በአግባቡ ይዞ ለሚፈለገው ልማት ለማዋል ጭምር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዲጂታል ካርታ ስርአቱን ከከተማው የስማርት ሲቲ ተግባራት ጋር በማቀናጀት በቅርቡ ከተጀመረው የዲጂታል የመኖሪያ ቤት መለያ ቁጥር አሰጣጥ ጋር በማስተሳሰር የሚፈጸም መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መምሪያው በጥናት የተለዩትን የባለይዞታዎች መረጃን ወደ ዲጂታል የመረጃ ስርአት በመቀየር ዲጂታል ካርታን ተደራሽ የማድረግ ስራውን በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም