የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮች ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት እያኖሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮች ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት እያኖሩ ነው
ሆሳዕና፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮችና አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት እያኖሩ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ በተያዘው ቀነ ቀጠሮ መሰረት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
የመራጮች የምዝገባ ሂደት ተጠናቅቆ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመገናኛ ብዙሀን አማራጭ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለህዝብ በማቅረብ የማስገንዘብ ሥራ እየሰሩ ነው።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገራቸው ምሁራን እንደገለጹት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊ፣ ተአማኒና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱና መቀጠል ያለባቸው ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው በሰላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑትና የፌዴራሊዝምና ህገ መንግስት ተመራማሪ ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር)፤ ጠቅላላ ምርጫውን ተአማኒ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ ተናግረዋል።
በተለይ ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ማድረጉ ሂደቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ ተአማኒነትን እና ተሳትፎን እንደሚያሳድግም አመልክተዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ መገናኛ ብዙሀን አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ክርክር ማድረጋቸው ህዝቡ ይሆነኛል ያለውን ፓርቲ ለመለየት ከማስቻል ባለፈ የዴሞክራሲ ሂደትን እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈጠረውን ምቹ ምህዳር በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው የገለጹት ተመስገን (ዶ/ር)፣ ህዝብና ሀገርን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሻግሩ አማራጭ ሀሳቦችን ይዘው ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ሳምሶን ወልዴ በበኩላቸው፣ ለ7ኛ ጊዜ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
ከምዝገባ ሂደት ጀምሮ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን ክርክር ህዝብ አውቆ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የሚዲያ ተቋማት እየሰሩት ያለውን ሥራ ለአብነት ጠቅሰዋል።
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሀዊና ተአማኒ ለማድረግ በገለልተኛነት የተሰየሙ ተቋማት እያከናወኑ ያለው ተግባር የዴሞክራሲ ሂደት አካል ስለመሆኑም መምህር ሳምሶን አንስተዋል።
የዴሞክራሲ ምህዳርን በማስፋት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ የተጀመረው ጥረት እንዲጠናከር የሁሉም ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።