የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን በባለቤትነት ለመምራት ያለመው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል።
ጉባኤው ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን የሰበሰበ ሲሆን፣ እነዚህ ግለሰቦች በድምሩ 321 ሚሊዮን የሚጠጋ ተከታይ አላቸው።
ተጽእኖ ፈጣሪዎቹ አዲስ አበባ ከትመዋል።
ከእነዚህም በተጨማሪ 150 ሚሊዮን ተከታዮች ያላቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች በጋራ በመሰባሰብ፣ በአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል አዲስ አበባ ላይ አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ ተዘጋጅተዋል።
ጉባኤው በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እና በኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል አዲስ አበባ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ የአፍሪካን ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደገና ለመቅረጽ ያለመ ነው።
ጉባኤው በአፍሪካ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሚሰበሰቡበት፣ ስለራሳቸውና ስለ አፍሪካ የሚናገሩበት፣ እንዲሁም ስለ ይዘት ፈጠራና በሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ይወያያሉ።
ይህም ተጽእኖ ፈጣሪዎቹን በአንድ መድረክ የማገናኛት ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሯል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በመጠቀም የይዘት ፈጣሪነት የወደፊት ሁኔታ፣ የአፍሪካ አዎንታዊ ገጽታን መገንባት እና የዲጂታል ተጽዕኖን ከአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ጋር ማጣጣም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሶስት የከፍተኛ ደረጃ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ጉባኤው "በችግር ላይ የተመሰረተ" ዘገባን በእውነተኛ የአፍሪካ የዕድገት ታሪኮች ለመተካት የታለመ ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑ ተመልክቷል።
የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ የማስተዋወቅ እድላቸው ሰፊ ነው።
እነዚህ የይዘት ውጤቶች የአፍሪካን መልካም ገጽታ ለዓለም፣ የኢትዮጵያንም መልካም ገጽታ ለአፍሪካውያን ማሳየት የሚችሉ ናቸው።
ጉባኤው በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚጀመር ሲሆን፣ ከ470 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል ተከታዮች አይኖች በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ላይ አርፈዋል።
ይህም አፍሪካ የራሷን ታሪክ ራሷ መተረክ የጀመረችበት አዲስ ዘመን ማሳያ ሆኗል፡፡