ኢትዮጵያ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስደንቅ ሥራ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስደንቅ ሥራ እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያስደንቅ ሥራ እየሰራች እንደሚገኝ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ገለጹ።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ጉባኤውም ከነገ ሚያዚያ 29 እስከ 30/2018 ዓ.ም "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄድ አህጉራዊ መድረክ ነው።
የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዳያስፖራዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጥሩበት መድረክም የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ አልሟል።
የ471 ሚሊዮን ተከታይ ባለቤት የሆኑ የ30 ሀገራት የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የጉባኤው ተሳታፊዎችም ከአራቱም የአህጉሪቷ ማዕዘናት ኢትዮጵያ አዲስ አበባ እየከተሙ ይገኛል።
በአጠቃላይ 321 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ሲሆን፤150 ሚሊዮን ተከታይ ያሏቸው 120 ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን የማህበራዊ ሚዲያ የይዘት ፈጣሪዎች ይቀላቀሏቸዋል።
አዲስ አበባ የገቡ የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አፍሪካ የሚነገሩ ብዝኅ እውነቶችና ፀጋዎች ሳሏት ዓለም በተሳሳተ ትርክት እንደሚረዳት ገልጸዋል።
ቦትስዋናዊው ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪ ዊሊያምላስት ኬአርኤም፤ በአስደናቂ ውበትና ዕድገት እየተጎናጸፈች የምትገኘው የአፍሪካዊያን መናገሻዋ አዲስ አበባ ሁለተኛ ቤቴ ናት ብሏል።
የአፍሪካን እውነተኛ ታሪክ ለዓለም ለመግለጥ በሚፈጥራቸው ይዘቶችም ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ ገልጿል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካን እውነት ለዓለም በመግለጥ አስደናቂ ሥራ እየሰራች ነው ያለው ዊሊያምላስት፤ ይዘት ፈጣሪዎችም የራሳችን ታሪክ በትክክል በማስተዋወቅ የተዛባ ትርክትን ማረም አለብን ብሏል።
ማህበራዊ ሚዲያ ታሪክን በራስ ድምፅ ከመናገር አንጻር ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥቷል።
ዑጋንዳዊቷ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አኳንጃ ኢስተር፤ የአፍሪካን የተሳሳተና የተዛባ ትርክት ለመቀየር የአህጉሪቷ ልጆች የሌላ ዓለም ነጋሪ እንደማያሻቸው ገልፃለች።
በጉባኤው ለመታደም አዲስ አበባ ከተማ በመገኘቷም ከአህጉሪቷ ወንድምና እህቶቿ ጋር ጠንካራ የትስስር ዕድል የምትፈጥርበት መሆኑን ተናግራለች።
አፍሪካዊያን ታሪካችንን በራሳችን እጆች ካልጻፍን ሌላው ወገን በተሳሳተ መንገድ ይከትብብናል ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ዑጋንዳዊት የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኒያኮ አካንጃ ናት።
የአፍሪካን አዎንታዊ ምስል ለዓለም ለማሳየትም የአህጉሪቱ ይዘት ፈጣሪዎች የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝባለች።
ጉባኤውም አፍሪካዊ ወንድምና አህትማማችነትን በማጠናከር እውነተኛ የአፍሪካ ትርክት ማስተጋባት የሚያስችል ወሳኝ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግራለች።
በተመሳሳይ የጉባኤው ተሳታፊ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ዑጋንዳዊው ኦንጅዮ ጆሾዋ፤ ጉባኤው የእርስ በእርስ ትውውቅን በመፍጠር ለጋራ ዓላማ መስራት የሚያስችል ነው ብሏል።
ኢትዮጵያም የአፍሪካን ታሪክ አተራረክ መስመር ለማስያዝ ጉባኤውን ማዘጋጀቷ ምስጋና የሚገባው መሆኑን ተናግሯል።