ቀጥታ፡

የአፍሪካን ተረክ የመቀየር አላማ በማንገብ በአዲስ አበባ የከተሙት የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን በባለቤትነት ለመምራት ያለመው የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል። 

ጉባኤው ከ30 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን የሰበሰበ ሲሆን፣ እነዚህ ግለሰቦች በድምሩ 321 ሚሊዮን የሚጠጋ ተከታይ አላቸው። 

ከእነዚህም በተጨማሪ 150 ሚሊዮን ተከታዮች ያላቸው 120 ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች በጋራ በመሰባሰብ፣ በአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል አዲስ አበባ ላይ አዲስ የዲጂታል ታሪክ ለመጻፍ ተዘጋጅተዋል።

ለዚህ ደማቅ መድረክ ታዋቂው ኡጋንዳዊ የቲክቶክ ኮከብ ሳድ ሶዚ (ቴንጌ ቴንጌ) ወደ መዲናዋ የገባ ሲሆን፣ ሌሎች የአህጉሪቱ የዲጂታል ድምጾችም አዲስ አበባ ደርሰዋል፡፡

ከኡጋንዳዋ ካዚንጋ መንደር በመነሳት በደማቅ የዳንስ ትርኢቶቹ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ቴንጌ ቴንጌ፣ ዛሬ ላይ ከመዝናኛ ባለፈ የሕፃናት መብት ተሟጋችና የማህበረሰብ ድምጽ ሆኖ ብቅ ብሏል።

የእርሱ በጉባኤው ላይ መገኘት፣ አፍሪካውያን የይዘት ፈጣሪዎች ከግል ዝና ባለፈ ለአህጉራዊ ልማትና ለዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ያላቸው ሚና ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

የጉባኤው አዘጋጆች እንደገለጹት፣ መድረኩ የይዘት ፈጣሪዎችን እንደ ተራ አዝናኞች ሳይሆን እንደ ባህል አምባሳደሮችና የለውጥ ወኪሎች እውቅና የሚሰጥ ነው።

ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ስለ አፍሪካ የሚነገሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን በመቀየር፣ ቱሪዝምን በማስፋፋትና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።

ለቴንጌ ቴንጌ እና ለጓደኞቹ ይህ ጉባኤ ከታዋቂነት በዘለለ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መድረክ ነው። 

ፈጠራን ከማህበራዊ ተፅዕኖ ጋር በማጣመር፣ የአፍሪካን ብዝሃነት፣ ጥንካሬና የወደፊት ተስፋ በራሳቸው በአፍሪካውያን አንደበት ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም