ቀጥታ፡

የአፍሪካዊው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣረ  ዎዴ ማያ - በአዲስ አበባ

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት ጉባኤ በአዲስ አበባ፣ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል። 

ይህ ጉባኤ ከሚያዚያ 29 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ አህጉራዊ መድረክ ነው።

የአህጉሪቷ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዳያስፖራዎች እና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጥሩበት ይህ መድረክ፤ የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ አልሟል።

ታዋቂው የአፍሪካዊ ዲጂታል ታሪክ ተራኪ ጋናዊው በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) ጨምሮ የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) በዲጂታል መገናኛ ብዙኅን የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክትና ገፅታ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ዓለም አቀፍ አንቱታን ያተረፈ የአህጉሪቷ የዘርፉ ፈርጥ ነው።

ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር ያለው ጋናዊው ታዋቂ ዩቲዩበርና የዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) አዲስ አበባ ገብቷል።

በጉባኤው ላይ የበርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) መገኘትም የአፍሪካን የዲጂታል ገፅታ መቀየር የሚያስችል የአህጉራዊ ይዘት ፈጠራ ትብብርን ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ይጠበቃል።

የአየር በረራ መሐንዲስ ስልጡኑ በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) የዲጂታል ታሪክ ተራኪነት ጉዞ በሀገረ ቻይና ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት ነበር የዩቱዩብ ይዘት ፈጠራን መሞከር የጀመረው።

የመጀመሪያዎቹ የዲጂታል ይዘት ፈጠራ ሥራዎቹም አስቂኝ የነበሩ ቢሆንም ወላጅ አባቱ የአፍሪካን በጎ ገፅታ ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለበት የሰጡትን ምክር ተከትሎ ጉዞውን ቀይሯል።

ባህላዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የቻይንኛ ቋንቋ ቪዲዮዎችን ያዘጋጅ የነበረው ዎዴ ማያ፤ ወደ ጋና ተመልሶ በሰራቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራዎቹ የሚፈለገውን ያህል ዕውቅና አላስገኙለትም ነበር።

መነሻውን በአዲስ አበባ በማድረግ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጉዞ በማድረግ አህጉሪቷን ለማስተዋወቅ ከሰራቸው ይዘቶች ውስጥ በሩዋንዳ የሰራው ቪዲዮ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ዕውቅናው እንዲናኝ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በእርሱ አተራረክ ማዕከላዊ ስፍራ እንዳላት የሚናገረው ዎዴ ማያ፤ የአፍሪካን ያልተነገሩ ስኬቶችና የአፍሪካዊያን ፅናት በተከታታይ ለዓለም ማስተዋወቁን ተያይዞታል።

አሁን ላይ የአፍሪካን ለውጥ፣ ተስፋና ዕድሎች ለዓለም ማህበረሰብ የሚያስተዋውቁ ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት የአህጉሪቷን ስሁት ትርክት በመቀየር ረገድ ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ሰዎች አንዱ ሆኗል።

በሚሊዮን የሚቆጠር ዕይታ ያላቸውን ዘጋቢ ፊልሞቹና የጉዞ ታሪኮችም ጊዜ ያለፈባቸው ስሁት ትርክቶችን በመሞገት የአፍሪካን ተስፋና ዕድሎች ለዓለም በመግለጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የኢትዮጵያን ዕድገትና ተስፋ ደጋግሞ የተረከው ዎዴ ማያ፤ በአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS) ወደ አዲስ አበባ መምጣቱም መድረኩን ተምሳሌታዊና ስልታዊ ያደርገዋል።

ይህም የበርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) የግል ጉዞ ከመሆኑም በላይ፤ ኢትዮጵያ የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ ፈጠራና የታሪክ አተራረክ ለውጦች ማዕከላዊ ሚና በተግባር ያስመሰክራል።

በዚህ ጉባኤ፤ እንደ ዎዴ ማያ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መሰባሰብ የአፍሪካን የዲጂታል ሥነ-ምኅዳር በማጠናከር ይዘት ፈጣሪዎች የአህጉራቸውን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ አለው።

ለኢትዮጵያም የዎዴ ማያ መገኘት ሀገሪቱ ለአፍሪካ ዲጂታልና ባህላዊ ሕዳሴ ያላትን ቁርጠኝነት የበለጠ በማሳደግ አዲስ አበባን የአፍሪካ የዲጂታል ገፅታ ግንባታ ሃሳቦች መነሻነት በተግባር ያረጋግጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም