ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተጠናክሯል

ጂንካ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት ወጣቶች በሀገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው መጠናከሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ።

የጂንካ ከተማ ወጣቶች ብልጽግና ፓርቲን የሚደግፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አለማየሁ ባውዲ እንደገለጹት፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ወጣቱ በማህበራዊ፣ በፖለቲካው እና በኢኮኖሚ ዘርፍ በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።


 

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ወጣቱ በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች በመሳተፍ ሀገር የመምራት ዕድል እያገኘ መጥቷል ብለዋል፡፡

ወጣቱ በሀገረ መንግስት ግንባታ የሚያደርገውን ንቁ ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት ገልፀው፣ በተለይ ብሔራዊ ጥቅምንና የሀገር ሉአላዊነትን በማስጠበቅ የወጣቱ አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን አመልክተዋል።

የሀገር ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እንዲፋጠንም ወጣቱ ራሱን በቴክኖሎጂ ከማብቃት ባለፈ የሚያገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም አለበት ብለዋል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፤ በወጣት የተገነባች ሀገር መሰረቷ ጽኑ እንደሆነ አንስተዋል።


 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ወጣቱ በልማት ሥራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በዚህም ወጣቱ በጥፋት ተግባር ከመሰማራት ይልቅ የልማት አርበኛ ሆኖ ለሀገራዊ ብልጽግና አሻራቸውን ማኖር መጀመሩን ገልጸዋል።

በሰልፉ የታደመው ወጣት እስራኤል አዳሙ፣ መንግስት ለወጣቱ በሰጠው ትኩረት በሁለንተናዊ መስኮች ተሳትፎውና ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን ተናግሯል።


 

ወጣት አዲሴ ምስሌ በበኩሉ፣ በአካባቢያቸው በሥራ ዕድል ፈጠራ ለወጣቱ ቅድሚያ መሰጠቱ ተጠቃሚነቱን እንዳሳደገው ነው የገለጸው።


 

በአሁኑ ወቅትም በርካታ ወጣቶች ሰርተው ሀብት ማፍራት እንደጀመሩ ጠቅሶ፣ ወጣቱ በሀገሩ ጉዳይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር አለባቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም