የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ወደ ሞሮኮ ያመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ወደ ሞሮኮ ያመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ 16ኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።
በአሜሪካዊው ቤንጃሚን ዚመር የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።
ቡድናችን አቋሙን ለመፈተሽ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የልምምድ ጨዋታ አከናውኗል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና የሥራአስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሜዳ በመገኝት ቡድኑን አበረታተዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ ልዑክ ዛሬ ከለሊቱ 10 ሰዓት ወደ አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ እንደሚያቀና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ መውጣቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ሞሮኮ፣ቱኒዚያ እና ግብጽ ጋር ተደልድላለች።
በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።