ቀጥታ፡

ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ገብረመስቀል ዱባለ እና ኪቲካ ጅማ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ስምኦን ማሩ የወልዋሎን ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ነገሌ አርሲ በ48 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

በሊጉም 12ኛ ድሉን አሳክቷል።

በውድድር ዓመቱ 11ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ35 ነጥብ ከነበረበት 13ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ዝቅ ብሏል።

ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡና 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ባህር ዳር ከተማ ፋሲል ከነማን 2 ለ 0 ረቷል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ፍጻሜውን አግኝቷል።

የ31ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከግንቦት 1 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም