ቀጥታ፡

ወጣቶች በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን ለማስቀጠል በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል

አምቦ ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ወጣቶች በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን ለማስቀጠል በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

የወጣቶች ተሳትፎ ለሰላማዊ ምርጫ በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአምቦ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሶምሳ እንዳሉት፤ በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን ለማስቀጠል በምርጫው የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ለዚህም ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ተአማኒና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ሚና የላቀ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ወጣቶች በከተማዋ ሰላምን በማፅናት ልማትን ለማስቀጠል እያደረጉ ያለውን የነቃ ተሳትፎ በምርጫው መድገም እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

የአምቦ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኩምሲሳ ቀጄልቻ በበኩላቸው፤ በለውጡ ዓመታት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራና የስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ወደ ተግባር የማስገባት ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ተግባሩን ለማስቀጠልም ወጣቶች በጠቅላላ ምርጫው በንቃት በመሳተፍ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአምቦ ከተማ ነዋሪዎቹ ወጣት ምትኩ ኩማ እና ወጣት ሌሊስቱ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ጠቅላላ ምርጫው ተዓማኒ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ እያከናወኑ ያሉትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም