በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያሳልጡ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በማየታችን ኮርተናል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያሳልጡ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በማየታችን ኮርተናል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያሳልጡ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በመመልከታቸው ኩራት እንደተሰማቸው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች እና አባላት ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች እና አባላት "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደውን አራተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ጎብኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚህ ወቅት፤ በኤክስፖው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያሳልጡ ተግባራት መከናወናቸውን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ስርዓት የምታደርገውን ግስጋሴ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ቴክኖሎጂዎችን ተመልክተናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዜጎችን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ምርታማነት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ በሰላም ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ምርቶችን ከውጭ የምታስገባ ሀገር ሆና መቆየቷን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ሀብትና የሰው ሃይል ማምረት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን መመልከታቸውን ገልጸው፤ በጉብኝታችን ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና ላይ እንዳለች ተገንዝበናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ጠቅላይ ጸሀፊ አባ አብርሃም ገብረማርያም፤ ኢትዮጵያውያን የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል ብለዋል፡፡
ትልውዱ ለአምራችነት ልዩ ትኩረት በመስጠት የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህሉን እንዲያዳብር የአባትነት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት ፓስተር ታሪኩ ብርሀኑ፤ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የምታደርገው ጥረት አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተኪ ምርቶችን በስፋት ማምረት ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገው ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን ያግዛልም ብለዋል፡፡