ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት የቀጣናውን እድገት የሚያፋጥን ነው

ዲላ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት የቀጣናውን እድገት የሚያፋጥን መሆኑን  ምሁራን ገለጹ።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ "የሀይል ጥገኝነትና መጭው ጊዜ" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱም የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ለቀጠናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር የራሱ ድርሻ ማበርከት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።


 

በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት በኖርዌይ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ላይፍ ሳይንስ የታዳሽ ሃይል ተመራማሪ ሳም አድራማላ (ፕ/ር)  ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ  ከውሃ፣ ከንፋስና ከሌሎች ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆኑ የታዳሽ ሃይል ልማቶች የሚደነቁ ናቸው።

ይህም የአፍሪካ ሃገራት የታዳሽ ሃይልን በጋራ አልምተው ለመጠቀም ለሚያደርጉት ጥረት መሰረት እንደሚሆን ጠቁመዋል። 

ለአብነትም ከውሃ ሃይል ኤሌክትሪክ በማመንጨት ለጎረቤት ሃገራት በሽያጭ ማቅረቧ የቀጠናውን ትስስር በማጠናከር እድገትን የሚያፋጥን መሆኑን ጠቅሰዋል።

የታዳሽ ሃይል ልማት የነዳጅ ጥገኝነትን በማስቀረት ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ሽመልስ ንጋቱ (ዶ/ር) ናቸው።

ኢትዮጵያ ከታዳሽ ሃይል ኤሌክትሪክ ማመንጨትና ከሃገር ውስጥ ፍጆታ አልፋ ለጎረቤት ሃገራት እያቀረበች መሆኑ ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር ተደማሪ አቅም ነው ብለዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ ይስሃቅ ሰቦቃ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከውሀ፣ ከንፋስና ከጂኦ ተርማል ከፍተኛ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ጠቅሰዋል።


 

በዘርፉ ያለውን ሀገራዊ አቅም በማሳደግ ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የኤሌክትሪክ መስመር በማይደርስባቸው አካባቢዎች በፀሃይ ሃይልና በሌሎች አማራጮች ለአርሶ አደሩ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አንስተው አውደ ጥናቱም የዚሁ ትብብር አካል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለታዳሽ ሃይል ያላትን ምቹ ስነ ምህዳር በአግባቡ ለመጠቀም የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሃብታሙ ተመስገን (ዶ/ር) ናቸው።

በተለይ ማገዶ አጠቃቀምን ከማሻሻል ጀምሮ ባዮጋዝን ጨምሮ ታዳሽ ሃይል በማመንጨት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በአውደ ጥናቱ ከስድስት በላይ የታዳሽ ሃይል የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን የሃገር ውስጥና የውጭ የዘርፉ ምሁራን ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም