የአህጉሪቱን የተሳሳተ ዓለም አቀፍ ትርክትና ዕይታ ለማረም ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም አለብን - ኢዜአ አማርኛ
የአህጉሪቱን የተሳሳተ ዓለም አቀፍ ትርክትና ዕይታ ለማረም ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም አለብን
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ልጆች የአህጉሪቷን የተሳሳተ ዓለም አቀፍ ትርክትና ዕይታ ለማረም ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም አለብን ሲሉ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ጉባኤውም ከሚያዚያ 29 እስከ 30/2018 ዓ.ም "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄድ አህጉራዊ መድረክ ነው።
የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዳያስፖራዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጥሩበት መድረክም የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ አልሟል።
የ471 ሚሊዮን ተከታይ ባለቤት የሆኑ የ30 ሀገራት የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የጉባኤው ተሳታፊዎችም ከአራቱም የአህጉሪቷ ማዕዘናት ኢትዮጵያ አዲስ አበባ እየከተሙ ይገኛል።
በአጠቃላይ 321 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው 61 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ሲሆን፤150 ሚሊዮን ተከታይ ያሏቸው 120 ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን የማህበራዊ ሚዲያ የይዘት ፈጣሪዎች ይቀላቀሏቸዋል።
የአህጉሪቷ ዕንቁዎችም የአፍሪካን ድምፅ በአፍሪካዊያን ዕይታ በማስተጋባት የሚተጋውን ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) የሚዲያ ተቋም ጎብኝተዋል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (POA) የአፍሪካን የተሳሳተ ትርክት ለማረም እየሰራ የሚገኝ አህጉራዊ ተቋም መሆኑም ይታወቃል።
ኢስዋቲኒያዊው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስልዋኔ፤ ለፐልስ ኦፍ አፍሪካ እንዳለው፤ የአህጉሪቷ ልጆች የአብሮነት ጉባኤ የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ አለው።
የአፍሪካ ልጆች የውጭ አካላት የአህጉሪቷን በማጠልሸት የሚስሉበትን የተሳሳተ ዓለም አቀፍ ስዕላዊ ዕይታ ለማረም ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም አለብን ብሏል።
አፍሪካዊያን የራሳችንን ታሪክ መፃፍ አለብን ያለው ስልዋኔ፤ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤም የራሳችንን ታሪክ በራሳችን መፃፍ የሚያስችል የትብብር ድምፅ ለመገንባት አቅም እንደሚፈጥር ተናግሯል።
ኢስዋቲኒያዊውና የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው ጎጎ ሲዋቲኒ በበኩሉ፤ አፍሪካዊያን የአህጉራችንን እውነተኛ ገፅታ በራሳችን ድምፅ ለዓለም ማስተጋባት ይጠበቅብናል ብሏል።
ጉባኤውም በአፍሪካዊያን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል የጋራ ግብና ርዕይ በመሰነቅ የአህጉሪቱን ድምፅ ለማስተጋባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግሯል።
በቀጣይም የአህጉሪቷ ልጆች ትብብር በማጠናከር ለአፍሪካ ዕድገትና የተሻለ ዕድል በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፏል።
ሴራሊዮናዊው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪው ቦይዜ ክሪሽ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነትና የአንድነት ተምሳሌት መሆኗን ገልጿል።
በፐልስ ኦፍ አፍሪካ አማካኝነትም የአፍሪካዊያንን ወንድማማችነት የሚያጠናክር ወሳኝ ስራ እየተሰራ መሆኑን በጉብኝቱ መገንዘቡን ገልጿል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ የአህጉሪቱን የማህበራዊ ሚዲያ ድምፆች የእርስ በዕርስ ግንኙነት በማጠናከር የጋራ ዓላማ መሰነቅ የሚያስችል ታላቅ ዝግጅት መሆኑን ተናግሯል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ የአህጉሪቷን በውበት ያሸበረቁ ብዝኅ ማንነቶች፣ ባህሎችና ውብ ተፈጥሮ ለዓለም ለማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ አለው።