ቀጥታ፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች ለዜጎች ፍትሕ ለማስፈን ወሳኝ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች ለዜጎች ፍትሕን በማስፈን ለሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ዘላቂነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በሕገ መንግሥት ትርጉም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣን፣ የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት ሚና ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሂዷል።


 

አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሕገ መንግሥት የሀገር የበላይ ሕግ ብቻ ሳይሆን ዜጎች በጋራ ለመኖር የተስማሙበት ቃል ኪዳንና የመንግሥት ስልጣን ገደብ የተቀመጠበት ሰነድ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሰጠው ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ስልጣን የግለሰብና የቡድን መብቶችን የሚያስከብር ውጤታማ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።

የውሳኔዎቹ የአስገዳጅነት ደረጃ ከውሳኔው በኋላ ለሚከሰቱ ሁሉም ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑና እንደ አንድ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እኩል ተፈፃሚነት እንዳላቸው አስረድተዋል።

ሆኖም ጥናቶች እንደሚያሳዩት የምክር ቤቱ ውሳኔዎች በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በተግባርና በመፈፀም ረገድ አሁንም ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።

በሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎች በሕገ መንግስቱ ይዘትና አፈፃፀም ላይ የሚሰጡ ትርጉሞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት የምክር ቤቱን የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች በመፈፀምና በማስፈፀም ዜጎች የሚገባቸውን ፍትሕ በማስገኘት ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዘላቂነት መሰረታዊ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔ አፈፃጸም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዳኝነትና ፍትሕ ተቋማት ለሀገርና ህዝብ ጥቅም መጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።


 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አበባ እምቢአለ፤ ማንኛውም አካል ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ የፍርድ ቤቶችም ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያገኘ ተመሳሳይ ጉዳይ በፍርድ ቤቶች ድጋሚ መታየቱ ዜጎችን ለእንግልት ይዳርጋል ያሉት ደግሞ የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም