የአፍሪካ ልጆች የራሳቸውን ታሪክ ለዓለም ለመንገር ውል የሚያስሩበት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ልጆች የራሳቸውን ታሪክ ለዓለም ለመንገር ውል የሚያስሩበት ጉባኤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ልጆች፣ የውጭ አካላት የአህጉሪቷን ስም በማጠልሸት የሚፈጥሩትን የተሳሳተ ዓለም አቀፍ ስዕላዊ ዕይታ ለማረም ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም ግድ የሚልበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አበባ የ2026ቱን የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS) ተሳታፊዎችን እየተቀበለች ትገኛለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5 እስከ 15 ሚሊዮን ተከታይ ያሏቸውን የአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የዲጂታል ታሪክ ተራኪዎች የሚያገናኘው መድረክ፣ ከቁጥር የተሻገረ ትልቅ ዓላማን ሰንቋል።
ጉባኤው ተጽዕኖ ፈጣሪነትን እውቅና ከመስጠት ባለፈ፣ አፍሪካ በዲጂታል ሥርዓት የራሷን ታሪክ በራሷ ልጆች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታስተዋውቅበት ወሳኝ አህጉራዊ የጋራ መድረክ ነው።
የቅድመ ጉባኤ የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ ማህበራዊ ሚዲያ የአፍሪካን ትክክለኛ ታሪክና ትርክት በአህጉሪቷ ልጆች ለዓለም ማህበረሰብ ለማድረስ እንደ ቁልፍ መሳሪያ ያገለግላል።
የአህጉሪቷ ልጆችም የውጭ አካላት የአፍሪካን ታሪክ በማጠልሸት የሚፈጥሩትን የተሳሳተ ስዕላዊ ዕይታ ለማረም ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው ነው ያረጋገጡት። የአህጉሪቱን ታሪክ ከውጭ በሚመጡ አካላት የሚቃኙበትን ስሁት ትርክት ለማስተካከልም መድረኩ ከውክልና የተሻገረ የተጽዕኖ፣ የቁጥርና የወደፊት አመለካከትን የሚቀርፅ መሆኑ ይታመናል።
የአፍሪካ ገፅታ ለበርካታ አስርት ዓመታት በውጭ መነፅር ሲታይበት የነበረውን የቀውስና አለመረጋጋት ስሁት ትርክት ለማስተካከል፣ የአህጉሪቷን ትክክለኛ መፃኢ ዕድልና ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያስችላል።
የዲጂታል ዓለም አዳዲስ ዕድሎችና ሰው ሰራሽ አስተውሎት የአፍሪካ ትክክለኛ ዕይታ ካልተካተቱባቸው፣ በአህጉሪቷ ላይ የተሳሳተ አመለካከትን መጫናቸው አይቀሬ ይሆናል።
የአዲስ አበባው የ2026ቱ የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤም፣ ተጽዕኖን ለመቋቋም አፍሪካ ይዘት ፈጣሪ ልጆቿን በአንድ ጥላ ሥር የምታሰባስብበት የትብብር መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የአህጉሪቷ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መሰባሰብም ከግል ስኬት ባሻገር የጋራ ስትራቴጂክ ዓላማን በማንገብ፣ በመቶ ሚሊዮን በሚቆጠር የተደራሽነት አቅማቸው አፍሪካን ለዓለም የሚያሳዩበት ትክክለኛ መነፅር ነው።
አዘጋጆቹና ባለድርሻ አካላትም የአፍሪካን በሕብር ያሸበረቀ ማንነትና መልካም ምኞት በመግለጥ፣ የተቀናጀ የታሪክ አተራረክ ምኅዳር ለመፍጠር በመልካም አጋጣሚነት ይጠቀሙበታል።
የፓን አፍሪካኒዝም ፋና ወጊዋ ኢትዮጵያም ጉባኤውን አዘጋጅታ ለማስተናገድ መወሰኗ፣ የአዲስ አበባን የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ስልታዊ መድረክ የስበት ማዕከልነት በተግባር ያረጋግጣል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ዕንቁዎች በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታም፣ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቷ ትርክት ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ይረዳል።
ይህም በሚሊዮን የሚቆጠር የዓለም ሕዝብ በአህጉሪቷ ይዘት ፈጣሪዎች አማካኝነት የኢትዮጵያን ዘመናዊ የከተማ ዕድገት፣ የባህል ሀብትና ትክክለኛ ገፅታ በአዲስ መልክ እንዲገነዘብ ያስችላል።
የ2026ቱ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS) አፍሪካ ከታሪክ ተገዥነት ወደ ታሪክ አቅራቢነት እየተሸጋገረች መሆኑን የሚያሳይ ነው።
የአዲስ አበባ ስብስብም የራስን ታሪክ የመንገር ኃይል እንደ ታሪኩ ራሱ ወሳኝ መሆኑን የሚያስታውስ ነው። በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ድምጿን አግኝታለች፤ ቀጣዩ ተግባር ደግሞ ይህ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ በልበ ሙሉነትና በጋራ ዓላማ መሰማቱን ማረጋገጥ ይሆናል።