በብሄረሰብ አስተዳደሩ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በብሄረሰብ አስተዳደሩ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው
ሰቆጣ ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የዝናብ አጠር የአየር ጠባይን ተቋቁሞ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ 113 ሚሊየን ብር በጀት መመደቡ ታውቋል።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ የመስኖ ተቋማትን በማስፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በዚህም ካሁን ቀደም የተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮም ተግባሩን ለማስፋት በ113 ሚሊየን ብር ወጪ የሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
በጋዝጊብላና ደሃና ወረዳዎች እየተገነቡ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶት 102 ሄክታር መሬት በማልማት 345 አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በደሃና ወረዳ የኢቤ ወንዝ የካናል ስራ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባቱን ጠቁመው በጋዝጊብላ ወረዳ የሚላና ዚባ ወንዝ የካናል ስራ በቀጣይ ወር እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ የዝናብ አጠር የአየር ጠባይን በመቋቋም የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልፀዋል።
በጋዝጊብላ ወረዳ የቀበሌ 03 ነዋሪ አርሶ አደር አገኘሁ ጌታሁን በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸው እየተገነባ ያለው የመስኖ ተቋም ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባም በክረምት ዝናብ ብቻ የተመሰረተውን የግብርና ልማትን በማሻሻል በመስኖ በመሰማራት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
በብሄረሰብ አስተዳደሩ ቀደም ሲል በተገነቡ የመስኖ ተቋማት 4 ሺህ 885 ሄክታር መሬት እየለማ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።