ቀጥታ፡

በከተማዋ በየዘርፉ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ በትጋት እንሰራለን- የብልጽግና ፓርቲ አባላት 

ደብረ ብርሃን ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት በደብረ ብርሃን ከተማ በየመስኩ በጀመራቸው የልማት ስራዎች የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ገለፁ።

“ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር'' በሚል መሪ ሀሳብ የብልጽግና ፓርቲ የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር በደብረ ብርሃን ዛሬ ተካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ብርሃኔ ስዩም እንደሚሉት፤ በደብረ ብርሃን ከተማ በመደመር እሳቤ የተከናወኑት የልማት ስራዎች ሁለንተናዊ ስኬት እንዲመዘገቡ ያደረጉ ናቸው።

የተጀመሩ የልማት ስራዎች ይበልጥ አድገውና ዳብረው የህዝብን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡም ለፓርቲው የሚያደርጉትን ድጋፍና እገዛ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።

ፓርቲው በከተማዋ እያከናወነ የሚገኘው ሰላምን የማፅናትና ልማትን የማረጋገጥ ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ያሉት ደግሞ አቶ መዝገቡ ተመኙ ናቸው።


 

መጪው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ  የተናገሩት ደግሞ ሌላው የምርጫ ቅስቀሳው ተሳታፊ አቶ በለጠ ወልደማሪያም ናቸው።

በተለይም በእጩዎችና በመራጮች ምዝገባ ወቅት የታየውን የነቃ ተሳትፎና እንቅስቃሴ በድምፅ አሰጣጡ ወቅትም እንዲቀጥል ተገቢውን እገዛ ለማድረግ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከተማዋ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ማዕከል እየሆነች መጥታለች ነው ያሉት።

መንግስት የከተማዋን እድገትና ደረጃዎች የሚያፋጥኑ አዳዲስ የመንገድ እና የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በማድረግ ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

ከተማዋን የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም