ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ነው

አዶላ ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ድርቅና የአካባቢ መራቆትን ለመቋቋም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ መጀመሩን  የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ እንዳሉት፤ በዞኑ ድርቅና የአካባቢ መራቆትን በዘላቂነት ለመቋቋም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ ተጀምሯል፡፡

በዞኑ ለደን፣ ለጥላ ዛፍ፣ ለፍራፍሬ ልማት፣ ለውበትና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ከ98 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ እስካሁን 27 ነጥብ 8 ሚሊዮኑ የበልጉን ዝናብ በመጠቀም በ6 ሺህ 726 ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ እየተተከሉ ያሉት ችግኞች ድርቅና የአካባቢ መራቆትን ከመቋቋም አልፎ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡

ቀደም ብለው የተተከሉ ችግኞች የእንስሳት መኖና የከርሰና ገጸ ምድር ውሀ አቅርቦትን በማሻሻል የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዞኑ አዶላ ወረዳ የዳማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ አሰፋ በበኩላቸው፤ በአካባቢያቸው የሚስተዋለውን የአካባቢ መራቆትና ድርቅ ለመከላከል በሚከናወኑ ተግባራት በንቃት መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።

ቀደም ብለው የለሙ አካባቢዎችን ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመከለል ለመኖ አቅርቦትና ለንብ ማነብ ስራ ላይ በማዋል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮ የበጋ ወራትም የማሳና የተራራ ላይ እርከን ስራ ላይ ከመሳተፍ ባለፈ በክረምቱ ወቅት የሚተከሉ ችግኞች ማፍላታቸውን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም