ለሀገር እድገት የተሻለ ሀሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ቀን እየተጠባበቅን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር እድገት የተሻለ ሀሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ቀን እየተጠባበቅን ነው
ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በምርጫ ካርዳቸው ለሀገር እድገት የተሻለ ሀሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ቀንን እየተጠባበቁ መሆናቸውን የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ በጠቅላላ ምርጫው ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመለየት በመገናኛ ብዙሀን የሚቀርቡ የፓርቲዎችን ክርክር እየተከታተሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመላ ሀገሪቱ ከ50 ሚሊዮን 514 ሺህ በላይ መራጮች ተመዝግበው ካርድ እንደወሰዱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸውን የፖሊሲና የፕሮግራም አማራጮችን በመገናኛ ብዙሀን ከማቅረብ ባለፈ ቅስቀሳዎችን እያደረጉም ይገኛሉ።
በምርጫው ላይ ኢዜአ በሚዛን አማን ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም በወሰዱት የምርጫ ካርድ ይሆነኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዘላለም ዜና ምርጫ ዴሞክራሲን ከምንለማመድባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ ይህን ዕድል ሳናባክን መጠቀም አለብን ብለዋል።
በወሰድኩት የምርጫ ካርድ ድምጼን ለሀገር ልማትና ሰላም መጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል ለምለው ፓርቲ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ነዋሪው፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የአንድ ሰው ድምጽ ትልቅ ዋጋ ስላለው ሁሉም በንቃት መሳተፍ አለበት ብለዋል።
እስካሁንም በመገናኛ ብዙሀን እየተካሄደ ያለው የፓርቲዎች የምርጫ ክርክርን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸው፣ በምርጫው ቀንም ለሀገር እድገት የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻያለሁ ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራም ከወዲሁ ለመለየት የፓርቲዎችን የክርክርና የቅስቀሳ መድረክ እየተከታተልን ነው፤ በምርጫው ቀንም ይሆነኛል ለምለው ፓርቲ ድምጼን እሰጣለሁ ያሉት ደግሞ አቶ ወልደሚካኤል ተሾመ ናቸው።
በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ ስላላት በምርጫው ቀን የመምረጥ መብቴን በመጠቀም አሻራዬን ለማሳረፍ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል ።
ወይዘሮ አፀደ አቱሞ የተባሉ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ በጠቅላላ ምርጫው ሀገር ለመምራትና ለማሻገር ብቁ ነው የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመሳተፍ ካርድ ወስዶ የምርጫውን እለት በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት አሻግሬ መቹል ነው።
የሀገርን ልማት በማፋጠን ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል ለሚለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጹን በመስጠት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግሯል።