ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የይዘት ፈጣሪዎች የአህጉሪቷን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ እንደ አምባሳደር እያገለገሉ ይገኛሉ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ አፍሪካውያን የይዘት ፈጣሪዎች የአህጉሪቷን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ እንደ አምባሳደር እያገለገሉ መሆናቸውን ታዋቂው ጋናዊ የይዘት ፈጣሪ በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) ገለጸ።

የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።

ይህ ጉባዔ ከሚያዚያ 29 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄድ አህጉራዊ መድረክ ነው።

የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዳያስፖራዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጥሩበት መድረክም የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ አልሟል።

ታዋቂው የአፍሪካዊ ዲጂታል ታሪክ ተራኪ ጋናዊው በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) ጨምሮ የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

ጋናዊው በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አክኮን (ዎዴ ማያ) አዲስ አበባ በገባበት ወቅት ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ የአፍሪካን የይዘት ፈጠራ ባለሙያዎች በአንድ መድረክ በተለይም በአዲስ አበባ ማግኘት እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡  

የይዘት ፈጣሪዎቹ በአንድ አዳራሽ ተገኝተው የአፍሪካን አጀንዳ ለቀሪው ዓለም ለማድረስ የሚያደርጉት ምክክር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል።

በተለይም እርሱ የሚያራምደው የአፍሪካ አጀንዳ አካል የሆነው "ፐልስ ኦፍ አፍሪካ" (Pulse of Africa) ለዓለም እንዲደርስ ትልቅ ተስፋ እንዳለው ተናግሯል።

የይዘት ፈጣሪዎች ለአፍሪካ ትልቅ የለውጥ ኃይል መሆናቸውን ጠቅሶ የአፍሪካ አዲስ የለውጥ አራማጆች እንደሆኑም አስገንዝቧል።

የምንሰራቸው ቪዲዮዎች ዓለምን የመለወጥ አቅም አላቸው ሲልም አክሏል።

ወደ አዲስ አበባ ለሦስተኛ ጊዜ መምጣቱን የገለጸው ታዋቂው ዩቲዩበር፣ ቀደም ሲል ስለ ከተማዋ በሰራው ቪዲዮ የከተማዋን ፈጣን ዕድገት የተመለከቱ ብዙዎች ውጤቱን ማድነቃቸውን ገልጿል።

የይዘት ፈጣራዎች ቱሪዝምንና የሀገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑንም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም