ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጉዞ የሚያፋጥኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጉዞ የሚያፋጥኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

"ትምህርትን በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በፈጠራና በኢንዱስትሪ ትብብር ማሳደግ" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው የምርምር፣ የፈጠራና የአውደ-ርዕይ ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ተጀምሯል፡፡


 

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ ሳይንሳዊ የፓናል ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ግኝቶች ለጉብኝት ቀርበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ያለውን ሰፊ ተሞክሮ በመጠቀም ለሀገር ግንባታ የሚሰጠውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

በትምህርት ዘርፉ የሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያፋጥኑ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ምርምሮቻችን የሕዝባችንን ችግር ሊፈቱ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው የሚያመነጫቸው እውቀቶችና የፈጠራ ሃሳቦች ወደ ተግባራዊ መፍትሄ እንዲቀየሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በዩኒቨርሲቲውና በኢንዱስትሪው መካከል ያለውን ቅንጅት በማጠናከር፣ የምርምር ውጤቶች በቀጥታ ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑበት ሥርዓት መዘርጋቱንም አረጋግጠዋል።

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ቋንቋዎች ጥናት ኮሌጅ ኤክስኪዩቲቭ ዲን የቆየአለም ደሴ (ዶ/ር)፤ አውደ-ርዕዩ በዋናነት በትምህርት፣ በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽንና በኢንዱስትሪ ትብብር ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ያለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን አዳዲስ ግኝቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ዲኑ፤ ትምህርት በዲጂታል አማራጮች ተደግፎ ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ እንዲሆን መስራት ዋነኛ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ትምህርት ከንድፈ-ሃሳብ ባለፈ የተማሪዎችንና የተመራማሪዎችን አቅም ወደ ተግባር የሚለውጥ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ይህ አውደ-ርዕይ በምሁራን፣ በተማሪዎችና በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበትና የወደፊት የትብብር መድረክ የሚፈጠርበት ታላቅ አጋጣሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም