ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በኢትዮጵያ መድን ተሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሳሙኤል ሳሊሶ በ83ኛው ደቂቃ ግቡን አስቆጥሯል።

በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና 55 ነጥብ ላይ ረግቷል።

ከተከታዩ መቻል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የማስፋት እድል መጠቀም አልቻለም። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፈም። 

በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ መድን በ37 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 11ኛ ከፍ አድርጓል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ መድን ከወራጅ ቀጠና አካባቢ በመጠኑ የራቀበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ፋሲል ከነማን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ብሩክ ሰሙ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ባህር ዳር ከተማ በ40 ነጥብ ከነበረበት 11ኛ ደረጃ ወደ 8ኛ ከፍ ብሏል። በሊጉ ስምንተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በሊጉ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በ43 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም