ቀጥታ፡

የሰራተኞችን መረጃ የማረጋገጥና ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል

ደብረ ብርሃን  ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ የማረጋገጥና ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመተባበር የሚያካሂዱት የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞችን መረጃ የማረጋገጥ ስራ ዛሬ ተጀምሯል።

የመምሪያ ኃላፊው ተወካይ አቶ ተሾመ ሸዋየ ለኢዜአ እንደገለጹት፤የመንግስት ሰራተኛውን መረጃ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት እየተካሔደ ያለውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለማፋጠን የሚያስችል ነው።


 

በተለይም የሰራተኛውን መረጃ በአግባቡ በመሰብሰብ፣ በመሰነድና ለአገልግሎት በማዋል ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ዲጂታል የመረጃ አሰባሰብ ስራው የሰራተኛውን መበትና ጥቅሙን በማስከበር  የስራ ተነሳሽነቱን ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ የሚገኙት 98 በመቶ የሚደርሱ የመንግስት ሰራተኞች ዲጂታል መታወቂያ ያወጡ መሆኑ ለተጀመረው ምዝገባ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ነው የገለጹት።

ከመንግስት ሰራተኞቹ መካከል አቶ አሰገደው ማሞ እንደገለጹት፤ የሰራተኛው መረጃ  ዲጂታላይዝ መደረጉ የፋይል ጥራትንና የመረጃ ብክነትን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል።


 

በተጨማሪም ህገ-ወጥ የሰራተኛ ዝውውር፣ ቅጥርንና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችን በማስቀረት የሰራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሌላኛዋ የመንግስት ሰራተኛ ወይዘሮ መዓዛ ግርማ በበኩላቸው፤በዘመናዊ መንገድ እንዲሰነድ የተደረገው  የሰራተኛው መረጃ በተገቢው መንገድ የስራ ገበታው ላይ ተገኝቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ይረዳል ነው ያሉት።


 

ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ዛሬ በዞኑና በወረዳዎች የተጀመረው የመረጃ ማጣራትና የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች የአካል ማረጋገጥ ስራ እስከ መጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም