የአፍሪካን ትክክለኛ ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅ የአህጉሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ትክክለኛ ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅ የአህጉሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን ትክክለኛ ታሪክ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የአህጉሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የሴኔጋል እና የቤኒን የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ገለጹ፡፡
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ጉባኤውም ከሚያዚያ 29 እስከ 30/2018 ዓ.ም "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄድ አህጉራዊ መድረክ ነው።
የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዳያስፖራዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጥሩበት መድረክም የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ አልሟል።
የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የጉባኤው ተሳታፊዎችም ከአራቱም የአህጉሪቷ ማዕዘናት ኢትዮጵያ አዲስ አበባ እየከተሙ ይገኛል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ሴኔጋላዊው የይዘት ፈጣሪ ጃው ኬቹን እና ቤኒናዊቷ የዲጂታል ተፅዕኖ ፈጣሪ ሬጂ ቦይዘር፤ ጉባኤው ለግንኙነትና ለልምድ ልውውጥ ወሳኝ የጋራ መድረክ ነው ብለዋል።
ሴኔጋላዊው የይዘት ፈጣሪ ጃው ኬቹን፤ ጉባኤው የአፍሪካዊያንን የቴክኖሎጂ፣ ባህል፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ድንበር ተሻጋሪ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጎበኝበትን ዕድል በማመቻቸት የአፍሪካን የዲጂታል ድምፆች በማቀራረብ የልምድ ልውውጥን እንደሚያጠናክር ተናግሯል።
በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ መምጣቱም የሀገሪቱን ባህልና ዕድሎች በማየት የአህጉሪቷን የይዘት ፈጣሪዎች የእርስ በዕርስ ትስስር እንደሚያጎለብት አንስቷል።
በአዲስ አበባ ለተደረገለት ደማቅ አቀባበልም ምስጋናውን አቅርቧል።
ቤኒናዊቷ የዲጂታል ተፅዕኖ ፈጣሪ ሬጂ ቦይዘር በበኩሏ፤ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ጉባኤ በአፍሪካ የዲጂታል ሥነ-ምኅዳር ውስጥ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን የሚያገናኝ ወሳኝ አህጉራዊ ተነሳሽነት መሆኑን ገልፃለች።
ጉባኤውም ከፍተኛ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችን፣ የፖሊሲ አውጪዎችንና መገናኛ ብዙኅንን በጋራ የሚያገናኝ መሆኑን ተናግራለች።
የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ማህበረሰብ ማስተዋወቅ የሚያስችል የግንኙነት ሥርዓት ለመፍጠርም ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስታለች።
የአፍሪካ ብርቅዬ የዲጂታል ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የጋራ መድረክም የአህጉሪቷን ትክክለኛ ትርክትና ዕድሎች ለዓለም ማህበረሰብ ለማስገንዘብ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
አዲስ አበባንም የአህጉሪቱ ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፋንታ የሚቀርጹ ውይይቶች ማዕከል ያደርጋታል።