ቀጥታ፡

የከተማዋን ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና ማህበራዊ እሴት በማልማት ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማዋል ተግባራት ይጠናከራሉ

ደብረ ማርቆስ ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የደብረ ማርቆስ ከተማን ባህል፣ ታሪክ ፣ ቅርስና ማህበራዊ እሴት በመጠበቅና በማልማት ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላከተ።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ገጽታን የሚገነባ፣ ቅርሶቿን በማስተዋወቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል "ሚያዚያን በማርቆስ" የተሰኘ  ፌስቲቫል ዛሬ ተካሄዷል።


 

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፤በከተማዋ የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችና ፀጋዎች በማስተዋወቅ ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

የከተማዋን ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና ማህበራዊ እሴት በመጠበቅና በማልማት ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

ይህም ቅርሶችና እሴቶች የቀድሞ ይዘታቸውን ጠብቀው ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ከማድረግ ባሻገር ጎብኚዎችን ለመሳብ ያስችላል ብለዋል።

ዛሬ የተካሄደው "ሚያዚያን በማርቆስ" የባህል ፌስቲቫል እና ፓናል ውይይት በከተማዋ የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን በመለየትና በማስተዋወቅ የሀብት ምንጭ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አእምሮ በበኩላቸው እንደገለጹት "ሚያዚያን በማርቆስ" የአካባቢውን ቱባ ባህል ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ነው።


 

ባለፉት አራት ዓመታት ፌስቲቫሉን በማካሄድ  የአካባቢውን ማህበረሰብ መስተጋብር በማጠናከርና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ወደ አካባቢው እንዲመጡ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ከቱሪዝም ልማቱ የሚገኘውን ዘላቂ ጥቅም ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ የከተማዋና የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የባህል አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም