ቀጥታ፡

ቅርሶች ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ሚና ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

መልካ ቁንጡሬ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦  በሀገሪቱ ያሉ ባህላዊና የተፈጥሮ ቅርሶች ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀንን በዩኔስኮ በተመዘገበው በመልካ ቁንጡሬ–ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ መካነ ቅርስ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል። 


 

ዕለቱ በዋናነት የቅርሶች ጥበቃና ለትውልድ ማስተላለፍ ያለውን ፋይዳ በሚያጎሉ ሁነቶች እየታሰበ መሆኑ ተገልጿል።

የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ ነው በመልካ ቁንጡሬ–ባልጩት መካነ ቅርስ እየተከበረ የሚገኘው። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ "የአፍሪካን ቅርሶች ማክበር፤ የነገ መሪዎችን ማብቃት" በሚል መሪ ቃል የተሰየመው ይህ ዕለት፤ በሀገራችን "የአፍሪካን ጥልቅ የሰው ልጅ ታሪክ ማክበር፤ የመልካ ቁንጡሬ–ባልጩት የአርኪዮሎጂና ፓሌኦንቶሎጂ መካነ ቅርስን መጠበቅ" በሚል መሪ ቃል በድምቀት እየታሰበ ነው።

በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ እንደገለጹት፤ ዕለቱን ማክበር በቅርስ ዙሪያ የወጡ ዓለም አቀፍ አዋጆችንና ደንቦችን ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ አለው። 


 

ይህም በሀገራችን ያሉትን ባህላዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ሚና ለማጎልበት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምርና ወጣቶች በቅርስ ጥበቃ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ ቀኑ በመልካ ቁንጡሬ እንዲከበር የተመረጠው፣ መካነ ቅርሱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበትን 2ኛ ዓመት ለማክበርና በቅርሱ አጠባበቅና አስተዳደር ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ለመወያየት ታስቦ መሆኑም ገልጸዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበሩ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ፋይዳ ለማስገንዘብ ይረዳል ብለዋል። 

በቅርሶች ላይ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች እንዲያድጉና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለውን የቅርስ ጥበቃ ትብብር ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥርም አክለዋል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደራራ ከተማ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በመልካ ቁንጡሬ የተገኙ የአርኪኦሎጂ እና የፓሊዮንቶሎጂ ውጤቶች ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛና የዓለም ሥልጣኔ ምንጭ መሆኗን በተጨባጭ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።


 

ቦታው የእንስሳት ቅሪቶች፣ የጥንታዊ ሰው የእግር አሻራ እና ከድንጋይ ዘመን ጀምሮ ያለውን የሥልጣኔ ማስረጃ የያዘ በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹት አቶ ደራራ፤ መንግሥት ለቅርሶች በሰጠው ልዩ ትኩረት መካነ ቅርሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊመዘገብ መቻሉን አስታውሰዋል።

የሚመለከታቸው አካላትና መላው ማኅበረሰብ እነዚህን ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ፣ ለሀገራዊ ብልጽግናና ለትውልድ መሸጋገሪያ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም