ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የብድር አስተዳደር ላይ በተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች በዕዳ ዕፎይታ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የብድር አስተዳደር ላይ በተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች በዕዳ ዕፎይታ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገለጹ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያዘጋጀው ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ሉዓላዊ ፋይናንስ ፎረም እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በፎረሙ መክፈቻ ላይ  የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እንደተናገሩት፤ የብድር ዕዳ አስተዳደር ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ ለልማት ስትራቴጂና ለፖሊሲ ተዓማኒነት መሰረት ነው።

በኢትዮጵያ ዕዳ አስተዳደር ላይ በተከናወኑ ወጤታማ ስራዎች የብድር ዕፎይታ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቡድን-20 የጋራ ማዕቀፍ ስር ትልቅ ምዕራፍ ላይ መድረሷን ገልጸው፤ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የብድር እፎይታ ጊዜ አግኝታለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማካሄድ ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት መሸጋገር፣ የገንዘብ ፖሊሲን ማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማሳደግ፣ በዕዳ አስተዳደር ግልጽነትን መፍጠር እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የዋጋ ግሽበትን መቀነስ፣ የወጭ ንግድ ገቢን ማሳደግ እና የውጭ ምንዛሬ ክምችትን በማሳደግ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር እና የንግድ መስመሮች እንዲስተጓጎሉ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በአፍሪካ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በአፍሪካ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት ​የብድር ወጪን መቀነስ፣ የሀገር ውስጥ እና ቀጣናዊ የፋይናንስ ገበያዎችን እና ​የዕዳ አስተዳደር አቅምን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የውጭ ፋይናንስ ጥገኝነትን ለመቀነስ የሀገር ውስጥ የምንዛሪ ቦንድ ገቢን ማሳደግ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ብድር የልማት እንቅፋት ሳይሆን የልማት መሣሪያ የሚሆኑበትን አሰራር ማስፈን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡


 

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀኃፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፋዊ የጅኦፖለቲካ ውጥረቶች የአፍሪካን የጸጥታና የንግድ ፍሰት በማስተጓጎል የሸቀጦችን ዋጋ አንሯል ብለዋል፡፡

ይሄውም የኢንቨስትመንት ፍላጎትን በመገደብና የካፒታል ዋጋን በመጨመር የአፍሪካን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት ገድቧል ብለዋል፡፡

የዕዳ ስልቶችን ከአየር ንብረት እና ከልማት ግቦች ጋር ማጣጣም ፣ ​ተቋማዊና የመረጃ ምንጮችን ማጠናከር፣ የተቀናጀ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም