ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጤና ችግሮች ላይ መፍትሄ የሚያመጡ ምርምሮችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጤና ችግሮች ላይ መፍትሄ የሚያመጡ ምርምሮችን እያከናወነ ነው
አዳማ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ አርሲ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለአካባቢው ማህበረሰብ የጤና ችግሮች መፍትሄ የሚያመጡ ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
በዩኒቨርሲቲው ስር የሚገኙ ሆስፒታሎችም ለአካባቢው ማህበረሰብ ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፍቃዱ ምትኩ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ የጤና ችግሮች መፍትሄ የሚያመጡ ምርምሮችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በጤና፣ በግብርና፣ በኢንጂነሪንግና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ ተግባር ተኮር ትምህርትን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በምርምር ስራዎቹ በተለይ በአካባቢው የጤና ችግሮች የሆኑትን ለይቶ የመፍትሄ አማራጮችን ከመጠቆም ባለፈ በአእምሮ ጤና፣ በጉሮሮ ካንሰር፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ጠለቅ ያሉ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በስሩ ከሚገኘው የአሰላ ሪፈራል ሆስፒታል በተጨማሪ አዲስ ያስገነባው የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል በዘንድሮ ዓመት አገልግሎት መጀመሩን አክለዋል።
በአሁኑ ወቅም በስሩ የሚገኙ ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝድ ማድረግ መቻሉንም ነው የገለጹት።
የዩኒቨርሲቲው የህክምና ዘርፍ ተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት ለመከታተልና የተለያዩ ምርምሮችን ለማከናወን በሆስፒታሎቹ ወስጥ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱም ነው የተናገሩት።
የዩኒቨርሲቲው የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል ዳይሬክተርና የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶክተር ጀማል ረሻድ፤ ሆስፒታሉ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን በተሟላ መልኩ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ የማህፀን ህክምናና የወሊድ አገልግሎት እንዲሁም የህፃናት ክትባትና የጨቅላ ህፃናት ህክምና አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ 200 አልጋዎች እንዳሉት ጠቁመው ከዚህ ውስጥም 70 የሚሆኑት ለጨቅላ ህፃናት ህክምና አገልግሎት እየዋሉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ በቀን በአማካይ ለ15 እናቶች የወሊድና ቀዶ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ሆስፒታሎቹ ከእናቶችና ህፃናት ህክምና በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን በዘመናዊ መልኩ እየሰጡ እንደሆነም ጠቁመዋል።