በዞኑ ለኩታ ገጠም እርሻና የግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠቱ ምርታማነታችንን እያሳደግን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለኩታ ገጠም እርሻና የግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠቱ ምርታማነታችንን እያሳደግን ነው
መቱ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በኢሉአባቦር ዞን ለኩታ ገጠም እርሻና የግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት በመስጠቱ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የመኸር እርሻ ዝግጅትን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ አርሶ አደሮች እንዳሉት የኩታ ገጠም እርሻና የግብርና ሜካናይዜሽንን በመተግበር ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ወደ ስራ ገብተዋል።
የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በወቅቱ በመቅረቡ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስና በማለስለስ በዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ገረሙ በዛብህ በመኸር እርሻ በበኩታ ገጠም ለሚያለሙት መሬት የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በወቅቱ በመቅረቡ የእርሻ ስራቸውን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮ በሰብል ልማት ምርታማነታቸውን ለመሳደግ የግብርና ሜካናይዜሽንና ኩታ ገጠም እርሻን በመጠቀም ለማልማት እየተዘጋጁ መሆናቸውን አንስተዋል።
ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ መቅረቡ መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ በዘር ለመሸፈን እንዳነሳሳቸው የተናገሩት ደግሞ በአሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ይርጋለም ጫሊ ናቸው።
ማሳቸውን በኩታ ገጠም ለማልማት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም ምርታማነታቸውን በመጨመር በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።
በኩታ ገጠም የሚያለሙትን መሬት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በትራክተር እያረሱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አበራ ተስፋዬ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረጉት ኩታ ገጠም ልማት ኢኮኖሚያ ተጠቃሚነታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገው መምጣቱንም ተናግረዋል።
በኢሉአባቦር ዞን በመኸር እርሻ 389 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አዳሙ ታከለ ናቸው።
በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረትም በመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት 81 በመቶው በኩታ ገጠም እንደሚታረስ ተናግረዋል።
በዞኑ የግብርና ሜካናይዜሽን መስፋፋትን ተከትሎ የአርሶ አደሩ በትራክተር የማረስ ልምድ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
በዞኑ በመኽር እርሻ ሩዝ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች እንደሚለሙ ገልጸው፣ ለልማቱ የምርት ማሳደጊያ ግብአት በወቅቱ የማድረስ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው ብልዋል።
በመኸር እርሻው ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች፣ ማሕበራትና ባለሀብቶችን በማሳተፉ ከ15 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቀዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል።