ቀጥታ፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው የምርጫ ክርክር በእውቀት ላይ ተመስርተን ደምፅ ለመስጠት ያግዘናል

ቦንጋ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው የምርጫ ክርክር በእውቀት ላይ ተመስርተን ደምፅ ለመስጠት ያግዘናል ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 24 ቀን እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባ ተጠናቅቆ፤ ፓርቲዎች በፖሊሲና ፕሮግራሞቻቸው ላይ ክርክር እያደረጉ ይገኛሉ።

በፓርቲዎቹ መካከል የሚደረገው ክርክር በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለህዝቡ በቀጥታ እየደረሱ ነው።

ይህን አስመልክተው በቦንጋ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው የምርጫ ክርክር በእውቀት ላይ ተመስርተን ደምፅ ለመስጠት ያግዘናል ብለዋል።


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ አየለ ሀይሌ ፓርቲዎቹ በተለያዩ ጉዳዮች ለይ የሚያደርጓቸውን ክርክሮች በተለያዩ  የሚዲያ አማራጮች እየተከታተሉ መሆናቸውንና ባገኙት ግንዛቤ ሀገር አሻጋሪ ሀሳብ የያዘውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።


 

ወጣት መቅደስ ከበደና መንግስቱ አለማየሁ የተባሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ምርጫ የሀገርና የሕዝቦችን መፃኢ እድል የሚወሰን ትልቅ ኩነት በመሆኑ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ይፈልጋል ብለዋል።


 

በተለይም ወጣቱ የወሰደውን ካርድ በአግባቡ ተጠቅሞ ነገውን የተሻለ ለማድረግ ይበጀኛል፣ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሻግራል ያለውን ፓርቲ መምረጥ እንደሚገባው መክረዋል።


 

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው የምርጫ ክርክር በሀገራችን የዲሞክራሲ ምህዳሩ እየሰፋ መምጣቱን ማሳያ ነው ያሉት የሀገር ሽማግሌው አቶ በየነ በቀለ፣ ይህም ለመራጩ ህዝብ ብዙ አማራጮችን ይዞ መምጣቱን ገልፀዋል።

በክርክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመረጥ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ የሚያወርዱትን ሀገር አሻጋሪ ሀሳብ ጨዋነት በተመላበት መልኩ ማቅረብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

እርሳቸውም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች እየቀረቡ ያሉትን የምርጫ ክርክሮች እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህም በመታገዝ በዕውቀት ላይ የተመሰረት ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም