ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካ መስኮች ንቁ ተሳታፊ የሆኑበት ዕድል ተፈጥሯል

ጂንካ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካ መስኮች ንቁ ተሳታፊ የሆኑበት ዕድል መፈጠሩን የጂንካ ከተማ ሴቶች ተናገሩ።

በለውጡ ዓመታት በብልጽግና ፓርቲና በመንግሥት በተለያዩ መስኮች ለተመዘገቡ አኩሪ ድሎች እውቅና የሰጠና የከተማው ሴቶች የተሳተፉበት የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

በድጋፍ ሰልፉ የታደሙ ሴቶችም ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር ለመጡ ተጨባጭ ውጤቶች ዕውቅና የሰጡ መፈክሮችን አሰምተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ የታደሙት የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አዳነች ሉሉ፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንና ለእዚህም ዕውቅና ለመስጠት በድጋፍ ሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው መስክ ንቁ ተሳታፊ የየሆኑበት እድል ተፈጥሯል ያሉት ወይዘሮ አዳነች፣ ለዚህም ተጠቃሚነታችን በማደጉ ዕውቅና እንሰጣለን ብለዋል።

ሌላዋ የሰልፉ ታዳሚ ወጣት ራሄል አበራ በበኩሏ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በብልጽግና ፓርቲ መሪነትና በመንግሥት በተከናወኑ ሥራዎች በተለያዩ ዘርፎች አንፀባራቂ ድሎች ተመዝግበዋል።

በተለይ የሴቶች እኩልነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው መረጋገጡን ጠቅሳ፣ ሴቶች በየመስኩ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ሀገር የሚመሩበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ከለውጡ ዓመታት ወዲህ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ወሰንየለሽ ካሳ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።

በእነዚህ ዓመታት ሴቶች በቁልፍ ቦታዎች ጭምር ተመድበው የመምራት አቅማቸውን ማሳየታቸውን ገልጸው፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነትም እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የመጡ ተጨባጭ ለውጦች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የገለጹት ወይዘሮ ወሰንየለሽ፣ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች እውቅና ለመስጠትና ድጋፋቸውን ለመግለጽ በሰልፉ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በጂንካ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የብልጽግና ፓርቲ እጩዎች የምረጡኝ ቅስቀሳም አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም