የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሆኖ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሆኖ ይቀጥላል
ሐረር፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
በሐረሪ ክልል ለሚገኙ አቅመ ደካማ ዜጎች የኑሮ መሻሻል ታስቦ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና ተጠሪ ተቋማት የተገነቡ 12 መኖሪያ ቤቶች ርክክብ ተከናውኗል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ 12 መኖሪያ ቤቶቹ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በተገኙበት ነው ዛሬ በይፋ ተመርቀው ለባለቤቶቹ የተላለፉት።
የግንባታው መጠናቀቅ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።
መንግሥት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸውን የልማት ውጥኖች በቁርጠኝነት እንደሚገፋበትም አረጋግጠዋል።
በተለይም በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ዜጎችን የመደገፍና የማገዝ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ አንስተዋል።
የመኖሪያ ቤቶቹ በአጭር ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ተገንብተው ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን እንዲተላለፉ በመደረጉም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ሚኒስቴራቸውና ተጠሪ ተቋማቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የአቅመ ደካሞችና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ችግር በማቃለል በኩል ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት መሆኑንም ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የእርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን ከማሳደግ ባለፈ ዜጎች ንጹህ መኖሪያ ቤትና ለኑሮ ምቹ አካባቢ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
በዚህም ሚኒስቴሩ የበኩሉን ለመወጣት 28 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የ12 አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን በመገንባትና አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት ማስረከቡን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የፈሳሽ ሳሙናና ዳቦ መጋገሪያ እንዲሁም ለዶሮ እርባታ የሚያገለግልና የስራ እድል የሚፈጥሩ ተጨማሪ ግንባታዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ነዋሪዎችና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።