ቀጥታ፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በሕዝቦች መካከል የበለጠ አንድነት፣ ፍቅርና አብሮነት እንዲጸና ይሠራል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሕዝቦች መካከል የበለጠ አንድነት፣ ፍቅርና አብሮነት እንዲጸና ይሠራል ሲሉ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ጉባዔ ያካሂዳል፡፡

የመጀመሪያው ጉባዔ በጥቅምት የሚደረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው የርክበ ካህናት ጉባዔ ከትንሣኤ በኋላ በዋለ በበዓለ ሃምሳ እኩሌታ፣ በዕለተ ረቡዕ የሚካሄድ ነው።

ምልዓተ ጉባዔው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት መካሄድ ጀምሯል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጉባዔው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሕዝቡን የበለጠ ወደ አንድነት፣ ፍቅር፣ ዘላቂ የጋራ ሰላምና ወደ ፈሪሃ እግዚአብሔር ማምጣት የጉባዔው ዓቢይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንዲችሉ እንዲሁም ለሕዝብ ደኅንነት ቤተ-ክርስቲያን የበኩሏን ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክራ መሥራት ይኖርባታል ሲሉም ተናግረዋል።

ምልዓተ ጉባዔው ወቅታዊና ወሳኝ ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ-ክርስቲያንና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም