በሐረር የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተከላ ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተከላ ስራ ተጀመረ
ሐረር፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በሐረር የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተከላ ስራ ተጀምሯል።
የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተከላ ስራውን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) አስጀምረውታል።
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በዚሁ ጊዜ የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያው በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በተለይም ትክክለኛ የመረጃ ግብዓት ከመስጠት አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።
የተከላ ስራው በአጭር ጊዜ እንዲከናወን የክልሉ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሪክተር በላቸው ፀሐይ፤ ቴክኖሎጂው መረጃን በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ተደራሽ ለማድረግ የላቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።
እንዲሁም 35 ኪሎ ሜትር ራድየስን በመሸፈን ትክክለኛ ልኬት የሚወስድና 24 ሰዓት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያው የመንገድ ዲዛይን፣ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ስራ ለሚያከናውኑ፣ የመሬት አጠቃቀምን በጥንቃቄ ለመቆጣጠር፣ ለይዞታ መረጋገጫና ለሌሎችም መረጃን መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያ ተከላው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መሆኑንም ተናግረዋል።