ቀጥታ፡

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻን በማልማት የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ28/2018(ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻን በማልማትና ከአካባቢው መስህቦች ጋር በማስተሳሳር ሀይቁን የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

የሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ልማት የዲዛይን ሥራ ተጠናቅቆ ዛሬ ለህዝብ ይፋ ተደርጓል።

ከንቲባው በዚህ ወቅት እንደገለጹት የሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ልማት ሀይቁን ለትውልድ በሚተርፍ መልኩ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል መሆኑንና ይፋ የተደረገው ዲዛይን በሀይቁ ላይ የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን አካቶ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከጥቁር ውሃ እስከ ታቦር ተራራ ድረስ የሚለማውና 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ልማት ከተማዋን በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ተመራጭ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።

ከተማዋ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ናት ያሉት ከንቲባው ሀይቁን በአካባቢው ካለው ታቦር ተራራ፣ ፍል ውሀዎች፣ ፏፏቴዎችና ከወንዶ ገነት ጋር በማስተሳሰር አልምቶ የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።

በሀይቅ ዳርቻ ልማቱ የጥቁር ውሀ አካባቢ፣ በተለምዶ ፍቅር ሀይቅ ተብሎ የሚጠራው የመዝናኛ ስፍራ፣ የሀዋሳ አሳ ገበያ እና አሞራ ገደል አካባቢ ተካትተው አብረው ይለማሉ ብለዋል።

የሀይቅ ዳር ልማት ሥራው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማማከር አገልግሎት በመስጠት እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።

ዲዛይኑን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀ መርሀ ግብር የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አብርሃም ማርሻሎ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ በየነ በራሳን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የከተማዋ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም