ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምድር መራቆትና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል በኩል ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምድር መራቆትና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል በኩል ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ያካሄደችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ በአካባቢ ጥበቃ በኩል ዓለምአቀፍ ትኩረትን የሳበ ለውጥ ማስመዝገብ ችላለች።

እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ልዩ ልዩ የችግኝ ዓይነቶችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ቀጥላለች።

ይህም የደን ሽፋንን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ያመጣ ሲሆን፤ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና የውኃ ሀብትን በመጠበቅ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።




መርኃ ግብሩ የፍራፍሬ ተከላን በማካተቱ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለዜጎች ሥርዓተ ምግብ መሻሻል የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የምድር መራቆትና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል በኩል ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ምርትና ምርታማነትን በተጨባጭ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰው ቀደም ሲል በዓመት በሄክታር ይታጠብ የነበረን 130 ቶን አፈር፣ አሁን ወደ 54 ቶን ዝቅ ማለቱንም ገልጸዋል።

በተለይም በበጋ ወቅት በሚከናወኑ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የአፈር መሸርሸርን መከላከልና የውኃ ሀብቶችን መጠበቅ ተችሏል ነው ያሉት።

በጥናት እንደተረጋገጠው የምርት እና ምርታማነት ማደጉን፣ የደን ሽፋን መጨመሩንና የአፈር መሸርሸር መቀነሱን የገለጹት አስተባባሪው፤ አረንጓዴ አካባቢዎችን በማስፋፋት ለኑሮ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።





ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በዓለም የምግብ ድርጅት እጅግ ውስን ፍራፍሬ ከሚያመርቱ ሀገራት መካከል ትመደብ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ለምግብነትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የችግኝ ጣቢያዎችን በማብዛትና ክትትልን በማጠናከር በመርኃ ግብሩ የሚተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች መጠንና ጥራት ላይ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በተለይም በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ዝግጅት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አምና 600 ሚየዮን የሚሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውን አውስተው ዘንድሮ ከዚህ በላይ እንደሚሆን አመልክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ፋይዳዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ የፍራፍሬ ምርቶችን ለውጭ ገበያ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ለገበያ ማዕከላት ማቅረብ የጀመሩ አርሶ አደሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

እነዚህን መልካም ተሞክሮዎች ይበልጥ ለማስፋት የክትትልና ድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የፍራፍሬ ምርቶች ማኅበረሰቡ አማራጭ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ በማድረግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም