ቀጥታ፡

ጉባኤው አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያላትን ውጤታማ ተሞክሮዎች ለሌሎች ሀገራት ለማካፈል ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያላትን ውጤታማ ተሞክሮዎች ለሌሎች ሀገራት ለማካፈል እንደሚያስችል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ገለጸ።

አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ከግንቦት 3 እስከ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ጉባኤውን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ አዲስ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ከግንቦት 3 እስከ 5 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው “አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለምአቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድም አብራርተዋል፡፡

መድረኩ አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያላትን ውጤታማ ተሞክሮዎች ለሌሎች ሀገራት ለማካፈልና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በጉባኤው ከሀገር ውስጥ፣ ከአፍሪካ ሀገራት እና ከሌሎች ክፍላተ ዓለማት የተውጣጡ ከ350 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት አስታውቀዋል።

ቀዳማይ ልጅነት ልማት ወደፊት ምርታማ፣ ጤነኛ እና የተሻለ ሰብዕና ያለው ዜጋ በማፍራት በኩል አይተኬ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ጉባኤው የአመራሮች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የአሰራር ሥርዓትና የሰው ኃይል ግንባታ እንዲሁም የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ማጠናከር በሚሉ አጀንዳዎች ዙሪያ እንደሚመክር ጠቅሰዋል።

ጉባኤው አዲስ አበባ በዘርፉ የጀመረችውን የልህቀት ጉዞ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም