ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የኃይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማዘመን የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማሻሻል ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት የኃይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማዘመን የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማሻሻል መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች በዋናነት በታዳሽ ኃይል (በውኃ፣ በንፋስና በፀሐይ) ላይ ያተኮሩ መሆናቸው፣ ሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጋር የተጣጣመ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለያዘችው ስትራቴጂ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዚህም የአህጉሪቱ የታዳሽ ኃይል ልማት ማዕከልነቷን ለማረጋገጥ በጀመረችው ጉዞ ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ውጤቶች አጠናክራ ቀጥላለች፡፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም፣ የአፍሪካ ሕብረትን የ2063 አጀንዳ ለማሳካትና አህጉሪቱን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የአይሻ 2 እና የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በስኬት ተጠናቅቀው ወደ ሥራ በመግባታቸው የሀገሪቱ የኃይል ማምረት አቅም ከ9 ሺህ 752 ሜጋ ዋት በላይ ደርሷል።




የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከከተሞች ዕድገት፣ ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ከዲጂታል ሽግግር ጋር በተያያዘ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዘመኑ የሚጠይቀውን ኃይል በማቅረብ የዜጎችን ፍላጎት ለማርካት የተጠናከረ የማስፋፊያና የማዘመን ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡

መንግሥት በለውጡ ዓመታት የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ማስፋፋትና ማዘመን፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መገንባት መቻሉን ገልጸዋል፡፡




በኢትዮጵያ 44 በመቶ የነበረው የኃይል ተደራሽነት ሽፋን ባለፉት ሰባት ዓመታት የኃይል መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ሽፋኑን ወደ 54 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከሰባት ዓመት በፊት ኃይል የማመንጨት አቅም 4ሺህ 462 ሜጋ ዋት እንደነበረ በማስታወስ፤ አሁን ወደ 9 ሺህ 752 ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸው፤ ግድቡ ለሀገራዊ የኃይል ማመንጨት አቅም ዕድገት ገንቢ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን ለመመለስ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት የሚመጥን የኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታና ማስፋፊያ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት መከላከል ከሁሉም አካላት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም